ልማት ባንክና የአርሶአደር የኢንቨስትመንት ብድር ጥያቄ

በቅድሚያ እንኳን ለ2016 አደረሰን፤ አዲሱ ዓመት የስራ የልማት ይሁንልን እላለሁ። ልማት ሲነሳ ፋይናንስብሎም ልማት ባንክ መነሳታቸው አይቀሬ ነው።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአገራችን የፋይናንስ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ  የሆነና ለአንድ ምዕተ ዓመት የዘለቀ የፋይናንስ ተቋም መሆኑ የታወቃል፡፡ ባንኩ ሲመሰረት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ ዜጎች በሥራ የሚገጥማቸውን የፋይናንስ ችግር እንዲቀረፍላቸው ለማስቻል ነው።

በቅድሚያ እንኳን ለ2016 አደረሰን፤ አዲሱ ዓመት የስራ የልማት ይሁንልን እላለሁ። ልማት ሲነሳ ፋይናንስብሎም ልማት ባንክ መነሳታቸው አይቀሬ ነው።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአገራችን የፋይናንስ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ  የሆነና ለአንድ ምዕተ ዓመት የዘለቀ የፋይናንስ ተቋም መሆኑ የታወቃል፡፡ ባንኩ ሲመሰረት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ ዜጎች በሥራ የሚገጥማቸውን የፋይናንስ ችግር እንዲቀረፍላቸው ለማስቻል ነው።

ባንኩ በተለያዩ ሥርዓቶች በአገሪቷ የኢኮኖሚ እንቅስቀሴ ውስጥ ዜጎች ተሰማርተው አስፈላጊው የፋይናንስ አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ሲሰራ የመንግሥትን የልማት አቅጣጫ ሲያስተገብር የቆየ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ባንኩ በረጅም ጊዜ ጉዞው በተለያዩ የኢኮኖሚ ሴክተሮች አበረታች ውጤት አስገኝቷል፤ የአገሪቷ ኢኮኖሚ እንዲያድግ አስችሏል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ልማት ባንክ የጥቂቶች መደለብያና ከመንግስት ፖሊስ አስፈፃሚነት ይልቅ የተደራጁ ቡድኖች እንዳሻቸው የሚዘርፉት ባንክ ነበር፡፡

በተለይ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ይዘው አንድም ዘለላ ምርት ሳያመርቱ በባዶ መሬት ብቻ  እንደልብ ከባንኩ  ገንዘብ ሲበደሩ የነበሩ አያሌ ግለሰቦች እንደነበሩ መንግስት ራሱ ያስታወቀው ጉዳይ መሆኑ የቅርብ ዓመታት ትዝታችን ነው፡፡

ከለውጡ በፊት የነበረውን ይህን አይነት የዘረፋ ዘዴ ከባንኩ ጋር ሳይመሳጠሩ መፈጸም መቼም ሊሞከር አይችልምና ችግሩ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም እንደነበር መገመት አይከብድም።

በሌላ በኩል አገራቸውንና እራሳቸውን ለመጥቀም ደፋ ቀና የሚሉ ሀቀኛ ባለሀብቶችና ተበዳሪዎች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተውና መስፈርቱን አሟልተው በተገቢው መንገድ ብድር ወስደው የሚሰሩ እንዳሉ መዘንጋት የለበትም።

የአገሪቷ አብዛኛው ኢኮኖሚ መሠረቱን የጣለው በዚሁ የግብርና ዘርፍ ላይ ቢሆንም ቅሉ አብዛኛውን ጊዜ ከልማት ባንክ ብድር ሲጠቀሙ የነበሩት በሠፋፊ እርሻ ስም የተሠማሩ ባለሃብቶችና ከቢሮክራሲው ጋር ከፍተኛ ትስስር ያላቸው አካላት ብቻ ሲሆኑ ሌላው አርሶ አደር ግን የበይ ተመልካች መሆኑ ገሃድ የወጣ ሀቅ ነው።

ባንኩ እስካሁን ድረስ ለአርሶ አደሩ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ቢባልም እንኳን ለሰፋፊ እርሻዎች ማለትም ለቡና ፣ ሻይ ቅጠል ማስፋፍያ፣ ለሠሊጥ አምራች ገበሬዎችና በሰፋፊ አትክልት እርሻ ላይ ለተሠማሩ ብድር ከመሥጠት ውጪ አዲሱን የመንግስት ፖሊስ የሚያግዝና አርሶአደሮችን የሚደግፍበት ሂደት ተግባራዊ አላደረገም፡፡

ምናልባት አርሶ አደሮችን ደግፌያለሁ ካለም ብልጭ ድርግም የሚል በቁጥር የተሰፈሩ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች ከማቅረብ ውጪ ለአርሶ አደሩ እያደረገ ያለው የብድር አቅርቦት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ባንኩ በቅርቡ ኢንተርፕረነሮችን መዝግቦ ካሰለጠነ በኋላ የባንኩ ፕሬዚዳንት ጭምር በእራሳቸው መሬት ይዘው አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉና በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ግለሰቦች አስፈላጊውን ብድር እንመቻቻለን ሲሉ መደመጣቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ይሁንና ባንክ በአነስተኛ ግብርና ዘርፍ ብድር ስጡኝ ብለው የሚመላለሱ አርሶአደሮችን ዛሬ ነገ እያሉ ከማጉላላት ባለፈ ምንም ተጨባጭ ውጤት አለማሳየቱን እኔው ራሴ ምስክር ነኝ።

እኔ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ለረጅም ግዜ በግብርና ስራ ላይ የተሠማራሁና በትምህርት ደረጃም በቂ ዝግጅት ያለኝ ነኝ፡፡

ይሁንና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግብርናን በተለመደወው መንገድ ማስቀጠሉ አድካሚ ነውና፤ ገበያ ተኮር ሥራ መሥራት በማስፈለጉ ግብርናን ማዘመንና ከመንግስት ፖሊስ አኳያ የሌማት ትሩፋት መርሃግብርን በሥራ ላይ ለማዋል ያስችለኝ ዘንድ ካለኝ የእርሻ መሬት ላይ 5 ሺህ ካሬ ሜትር በመቀነስ የኢንቨስተመንት ፍቃድ አውጥቻለሁ።

በተጨማሪ ልማት ባንክ ከእኔ የሚፈልገውን 25 በመቶ መስፈርት አሟልቼ፤ በተዘጋጀው የባንክ መሥፈርት መሠረት በወተት ላም ርባታ ላይ ለመሳተፍ እንድችል ለባንኩ የብድር ጥያቄ አቅርቤያለሁ።  

ይሁንና ይህንን ጥያቄ ያቀረብን እኔና እኔን መሰል አርሶአደሮች ልማት ባንክ ሊያስተናግደን ፍቃደኛ ባለመሆኑ ለወራት እየተጉላላን እንገኛለን፡፡ ለዚህም ባንኩ ያቀረበው መልስ ብድር ስትወስዱ የወተት ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አብራችሁ ካልጠየቃች ለላሞች ግዢ ብቻ ብድር አንሰጥም የሚል ተልካሻ ምክንያት ነው።

እኛም በቅድሚያ የወተት ምርት ሳይኖረን እንዴት ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚፈልገውን የወተት ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መክፈት እንችላለን?፤ ይህስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና እኛ አርሶአደሮች ነን እንጂ ባለሃብት አይደለንም፤ ወደፊት አቅም ስንፈጥር ፋብሪካ እንገነባለን የሚል ምላሽ ከሌለሎች ጓደኞቼ ጋር ሰጥተናል።

ይሁንና ለአርሶአአደሮች የተገባው የብድር ድጋፍ ተሰርዞ ለሊዝ ፋናንስ ብቻ ነው ብድር የምንሰጠው የሚል አሳዛኝ ምላሽ ተሰጥቶናል።

በአንድ በኩል ማንም ሰው ፕሮጀክት ይዞ ከመጣ 25 ከመቶውን  የብድሩን ድርሻ ካዋጣና የመሥሪያ ቦታ ካለው እንዲሁም ፕሮጀክቱ አዋጭ መሆኑ ከታመነበት ብድር እናዘጋጃለን እያለ በየጊዜው መግለጫ የሚሰጠው  ባንኩ፤ ጥያቄ ሥናቀርብለት ግን ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ካልገነባችሁ ብድር አልሠጥም ማለቱ ምናልባት ማሽኑን ከሚሸጡት ጋር ቀጥተኛ ስምምነት ያላቸው ያስመስልባቸዋል፡፡

ለዚህም ነው በልማት ባንክ ትኩረት ያልተሠጠው ዘርፍ ግብርና ነው በሚል ቅሬታዬን ላቀርብ የተገደድኩት።

አብዛኛው በከተሞች ዙሪያ ያሉ አርሶአደሮች በወተትና በዶሮ ርባታ ላይ ቢሳተፉ ውጤታማ ከመሆናቸውም በላይ የመስሪያ ቦታ ችግር የማያጋጥማቸውና በቀላሉ የቤተሰብ ጉልበት በመጠቀም እራሳቸውንና አገራቸውን ሊጠቅሙ እንደሚችል ግልጽ ነው።

በርካታ የአርሶአደር ልጆች አሁን ላይ  ከዩኒቨርሲቲውም ይሁን ከኮሌጅ  ተምረው ሥራ በመፈለግ ላይ ናቸው፤ ይሁንና ባንኩ ከአርሶአደሮች የሚቀርብለትን የአነስተኛና ጥቃቅን ብድር  ፕሮጀክቶች ላይ ሳያጉላላ የብድር አቅርቦቱን ቢያመቻች አርሶአደሮቹም ልጆቻቸውን ይበልጥ ምርታማ ማድረግና የስራ ዕድል ፈጠራውን ማጠናከር ይቻል ነበር።

ልማት ባንክ አሁን የያዘው አቋም በግብርናው ዘርፍ ለሊዝ ፋይናንስ ብቻ ነው የማበድረው የሚለው አካሄድ ከዋናው የባንኩ ማዕከል ጀምሮ ሊጠናና የቅርንጫፎች አሰራርም ሊፈተሽ ይገባዋል።

በቂ የስራ ቦታ ለሌላቸው ሰዎች ብቻ ትኩረት እያደረገ እኛ የመሥሪያ ቦታ ያለን አርሶ አደሮች ፕሮጀክት ፋይናንስ አቅርበን ለመቀበል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ከበር እየመለሱን ስለመሆኑ እኔው እራሴ ምስክር ነኝና ችግሩ በአፋጣኝ ሊስተካከል ይገባል ባይ ነኝ።

በመጋቢት ወር 2015 ለልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያስገባሁት የግብርና ኢንቨስትመንት ብድር ማመልከቻ ዛሬ ነገ እየተባለ እስከ ዛሬ ድርስ መልስ አለማግኘቱን እይወቅኩ፤ በጎን ደግሞ  የባንኩ ሰዎች እኛ ጋር የቢሮክራሲ መንዛዛት የለም እያሉ ጠዋትና ማታ በቴሌቪዥን እና በጋዜጦች  መልስ ሲሠጡ ሳይ፤ ለእኑሱ እያፈርኩ ነው።

ምናልባታ እኔ በድፍረት ሃሳቤንና ቅሬታዬን የመግለፅ አቅም ቢኖረኝም እንደኔ ሃሳባቸውን ለመግለፅ አቅም የሌላቸውና ከልማት ባንክ ቅርንጫፎች ወደ ቤታቸው የተመለሱ አርሶ አደሮችን ብዛት ቤት ይቁጠረው፡፡

በራሱ መሬት ላይ ለወተት ላምም ሆነ ለዶሮ ለማርባት ፕሮጀክት አዘጋጅቶ የቀረበና ከልማት ባንክ ድጋፍ አገኛለው ብሎ የሚያስብ አርሶአደር ችግሩን መንግስት ተመልክቶ መመሪያ ካልሠጠ በስተርቀር በልማት ባንክ በኩል ተገቢውን ድጋፍ አገኛለሁ የሚከለው ተስፋው የተሟጠጠ ሆኗል፡፡

ለማጠቃለያ ያህል የተከበሩ የባንኩ ፕረዝዳንትም ሆኑ የሥራ አጋሮቻችው ግብርና ማዘመንና ገበያ ተኮር ምርት ማምረት ብዙ ሥራ አጦችን ከመደገፍ ባለፈ የመንግስትን ጫና እንደሚቀንስና፤ የመንግስትን የልማት ፖሊስ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተገንዝበው ሊሰሩ ይገባል።

በመሆኑም ትኩረት ለተነፈገጋቸው ለግብርና ዘርነና ለአርሶ አደሩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊው የፋይናንስም ሆነ የቴክኒክ ድጋፍ እስካልተደረገ ድረስ ባንኩ እየተጓዘበት ያለው መንገድ በስህተት የተሞላ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊገነዘብ ይገባል።

መንግስትም ባንኩ በአርሶአደር ኢንቨስትመንት ላይ ያለውን አሰራር በፋጣኝ በማስተካከል የአገሪቷን ኢኮኖሚ ይበልጥ ሊያነቃቃ ይገባል የሚል መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ለኢትዮጵያችን ለዘላቂ ዕድገቷ የፋይናስን አቅርቦት ወሳኝ ድርሻ አለው። ቸር እንሰንብት!

netevm.com