ሕብረት ባንክ ከኤምፔሳ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ፈረመ

ሕብረት ባንክና ኤምፔሳ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ለማከናወን ስምምነት አድርገዋል

ሕብረት ባንክ ዛሬ በዋናው መስሪያ ቤቱ ከሳፋሪኮም ኤምፔሳ ኢትዮጵያ  ጋር የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት መሥጠት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል።

የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መላኩ ከበደ እና የሳፋሪኮም ኤምፔሳ ኢትዮጵያ ጄነራል ማናጀር ፓውል ካቫቪ ስምምነቱን ፈጽመዋል።

በስምምነቱ ወቅት የሕብረት ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ መላኩ ከበደ ፤ የባንኩን የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚያግዝ ስምምነት መከናወኑን ይፋ አድርገዋል።

ሕብረት ባንክ ከሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ጋር የኤምፔሳ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ለመስጠት ባካሄደው የውል ስምምነት መሰረት ለደንበኞቹ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሠራም ነው አቶ መላኩ የተናገሩት።

ባንኩ የደንበኞቹን አገልግሎት ይበልጥ ለማቀላጠፍና የቅርንጫፍ ቢሮ በሌለባቸው የገጠራማ አካባቢዎች በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቱ ተደራሽ መሆን እንዲችል በኤምፔሳ በኩል የሚቀርበው የሞባይል ባንኪንግ ስርዓቱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

በስምምነቱ መሰረት የሕብረት ባንክ የገንዘብ አካውንት ያለው ማንኛውም ተገልጋይ ለሚገዛው ዕቃ ወይንም ደግሞ መክፈል ለሚፈልገው አገልግሎት ክፍያውን በቀላሉ በኤምፔሳ መፈፀም እንደሚችል ነው የተገለጸው።  

ኤምፔሳ በኬንያ ዲጂታል የፋይናስን አገልግሎት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን፤ አሁን ላይ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኩል ወደሀገር ውስጥ መምጣቱ የሚታወስ ነው።

ሕብረት ባንክ በጥር ወር 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘውን ዋና መስሪያ ቤቱን ባስመረቀበት ወቅት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።

ሕብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር “ሕብር ኢ-ኮሜርስ” የተሰኘ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት በማስተዋወቅ በስራ ላይ ማዋሉ የሚታወስ ነው።

netevm.com