ሙስና በቤተክርስቲያኗን ጓዳ

ከሰሞኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ዘመቻ የተጀመረበት ሙስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጓዳ ተገኝቶ እርምጃ መወሰድ መጀመሩ ተገልጿል። 14 ሰዎችም ታግደዋል።

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተ የሰየማቸውን አጣሪ ኮሚቴና ኦዲተሮች ያቀረቡትን ሪፖርት በማድመጥ  የሀገረ ስብከቱን ምክትል ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ 14 የክፍል ኃላፊዎችን በማገድ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ማሳለፉን ታውቋል።

አጣሪ ኮሚቴውና ኦዲተሮቹ ለአስተዳደር ጉባኤው ባቀረቡት የማጣራትና የኦዲት ሪፖርት መሠረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያመለክት ሲሆን ሀገረ ስብከቱ በተቋም ደረጃ ጉልህ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚታይበት፣ የሙስና ተግባራት የተንሰራፋበት፣ ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ መሥራት የማይታሰብበት ተቋም መሆኑን ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

በማጣራት ሪፖርቱ  ላይ እንደተገለጸው ሀገረ ስብከቱ  ከሕግ መተላለፍ፣ከሰበካ ጉባኤ ምርጫ፣ ከሠራተኛ ቅጥርና ዝውውር ፣ አዲስ ከሚተከሉ አብያተክርስቲያናት ፣ ከሠራተኞች እግድ ፣በሌላ ሀገረ ስብከት በበጀት ተመድበው የሚሠሩ ሠራተኞች በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአድባራትና ገዳማት መመደባቸውን ተገልጿል።

በአድማ በሕውከትና ግርግር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎችን የማዕረግ ስም በመስጠት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት እንዲመደቡ መደረጋቸው፣በአሮጌው ቄራ በመገንባት ላይ የሚገኘው ሕንጻ የጨረታ ሒደት ሕግን ያልተከተለና አጠራጣሪ መሆኑ  በተመለከተ ወዘተ  የሚሉት ከቀረበው ሪፓርት መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።

በተጨማሪም በሪፖርቱ ላይ  አጋዥ የሆኑ 1ሺ977 ማስረጃዎችም አባሪ ሆነው ተያይዘው ቀርበዋልም ተብሏል፡፡

ስለሆነም አስተዳደር ጉባኤው በቀረበው ሰነድ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል።

1. የማጣራት ሠነዱ በህግ አገልግሎት መምሪያ በኩል በሕግ ባለሙያዎች ተመርምሮ በሕግ የሚያስጠይቁና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ውሳኔ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ተለይተው እንዲቀርቡ፤

2. በማጣራት ሂደቱ  ላይ  ተጠያቂ  ሊሆኑ  ይገባቸዋል የተባሉ ምክትል ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ (፲፬)14 የክፍል ኃላፊዎች ጉዳያቸው በዝርዝር ታይቶ ውሳኔ እከሚሰጥበት  ጊዜ ድረስ  ከዛሬ ታኅሣሥ ፮  ቀን ፳፻፲፭ (ታህሳስ 6 2015 ዓ.ም) ጀምሮ  ደመወዛቸውና ጥቅማ ጥቅማቸውን እያገኙ ከሥራ እንዲታገዱ፤

2. ከዚህ በፊት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እውቅና ውጪ በሌሎች ማተሚያ ቤቶች ይታተም የነበረው ሞዴላ ሞዴሎች ከዛሬ ጀምሮ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት አሳታሚነት በትንሣኤ ማተሚያ ቤት ብቻ እንዲታተሙ፤

3. በወቅታዊ ጉዳይ ምክንያት ከሥራ ቦታቸው ታግደው በሥራቸው ሌሎች እንዲመደቡ የተደረገበት ሂደትን እጅጉን የኮነነው አስተዳደር ጉባኤው  በሕግ አገልግሎት መምሪያ በኩል በሚቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት በሚገባ ተጣርቶ የውሳኔ ሀሳብ እንዲቀርብ፤

 በመጨረሻ በአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችንና በቀጣይ በሀገረ ስብከቱ የሚመደቡ ሠራተኞችን በተመለከተ ተገቢውን ጥናት በማድረግ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.