ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘውና የቀድሞው ጠ/ሚ ፍርድ ቤት የቀረቡበት የክስ ሂደት

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከ111 የራዳሮች ግዢ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ሰሞኑን ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።

ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑት የቀድሞው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በሁመራ በኩል ወደሱዳን ለማምለጥ ሲሞክሩ ነው ህዳር ወር መጀመሪያ ሰሞን 2011 ዓ.ም ላይ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው በሄሊኮፕተር ወደአዲስ አበባ እንዲመጡ የተደረገው።

ከዚያም የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ላይ ጥራቱን ያልጠበቀ 111 ራዳር ከ214 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመግዛት በመንግስት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሎ በአራት ተከሳሾች ላይ ነበር የመንግስት ስራን በማያመች አኳኃን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ከሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተጨማሪ ሌተናል ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት፣ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታና የስነምግባርና የህግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሀን አብርሃ ክስ ቀርቦባቸዋል።

ክሱ ከቀረበ በኃላ ግን የሜጀር ጀነራል ክንፈና የኮሎኔል መሐመድ ብርሀን መዝገብ ብቻ የቀጠለ ሲሆን የሌሎቹ ክስ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጧል።

ተከሳሾቹ በ2004 ዓ.ም ያለጨረታ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የግዢ ፍላጎት ሳይጠይቅ ሴሌክ (CELEC) እና አሊት (ALIT) ከተባሉ የቻይና ኩባንያዎች ተመሳሳይነት ያላቸውን 111 ራዳሮች መግዛታቸውንና ራዳሮቹ አገልግሎት ሳይሰጡ መቀመጣቸው ክስ ያስረዳል።

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ስምስት የሰውና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ካቀረበ በኋላ ችሎቱ የምስክር ቃልና ማስረጃዎችን መርምሮ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተከሰሱበት በወንጀል ህግ አንቀጽ 32 /1 ሀ እና አንቀጽ 411 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።

ሜጀር ጀነራል ክንፈ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና የቀድሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሳሞራ የኑስን ጨምሮ ከአምስት በላይ የሰው የመከላከያ ምስክሮችንና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበው ነበር።

በተከሳሹ የቀረቡ የመከላከያ ማስረጃዎችን የመረመረው ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸውን አብራርቷል።

በወንጀለኛ መቅጪያ ስነ-ስርዓት ሕግ ቁጥር 149/1 መሰረት የጥፋቸኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸው ነበር።

ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበውን ወንጀሉ የተፈጸመው በጋራ በመሆኑ ቅጣቱ ከብዶ እንዲታይለት ያቀረበውን አስተያየት ሳይቀበል ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ አብረዋቸው ተከሰው የነበሩ ክስ የተቋረጠላቸው ግለሰቦች መኖራቸውን በመጥቀስ እንዲሁም ጉዳያቸው ተነጥሎ ሲታይ የነበሩ ተከሳሾች መኖራቸውን በማብራራት በህብረት የተፈጸመ ለማለት አያስችልም በማለት የዐቃቤ ህግ ማክበጃን አለመቀበሉን ገልጿል።

የሜ/ጀ ክንፈ ዳኘውን አምስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ግን ፍርድ ቤቱ ይዟል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ የሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በዕርከን 16 መሰረት በ3 አመት ከ7 ወራት ጽኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ ሜ/ጀ ክንፈ በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ ከስር መፈታት ይችላሉ ያለ ቢሆንም ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ያላጠናቀቋቸው ክሶች ማለትም ከዕርሻ መሳሪያ ግዢ፣ የመርከብ ግዢ፣ ከሆቴልና ከትምህርት ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ በአራት መዝገቦች ገና በፍርድ ቤቱ በመታየት ላይ ናቸው።

በዚሁ ተመሳሳይ የራዳር ግዢ የሙስና ወንጀል ክስ ጋር ተያይዞ ተከሰው የነበሩትና በዚሁ ፍርድ ቤት በ5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩት የሜቴክ የህግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሀን አብርሃ የቀረበባቸውን ክስ በተገቢው ተከላክለዋል ተብለው በነጻ መሰናበታቸው ይታወሳል።

netevm.com