የደቡብ ክልል ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የህዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት እየተከናወነ ነው ፡፡
ሕዝበ ውሳኔው በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያካሄደ ባለው የሕዝበ ውሣኔ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው መራጮች ድምጽ በመስጠት ላይ መሆናቸውንና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ችግሮች መታየታቸውን አስታውቋል።
ቦርዱ በተለያዩ የመርጫ ጣቢያዎች ላይ እያደረገ ባለው ክትትል መሰረት የደረሰባቸው ግኝቶች እና የወሰዳቸው እርምጃዎች ዘርዝሯል።
በ9 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተለያዩ የምርጫ ቁሳቁስ ጉድለት ሪፓርት የተደረገ ሲሆን ይህንኑ ለመቅረፍ በምርጫ ማእከል ደረጃ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ነው ያሳወቀው።
በ38 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለድምፅ መስጫ ቀን ከተመደቡ ተጨማሪ አስፈፃሚዎች ውስጥ በድምፅ መስጫ ቀን በጣቢያዉ ያልተገኙ በመኖራቸው ቦርዱ ይህንኑ ለማስተካከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
የድምፅ መስጫ ወረቀት ጉድለት በተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ 11 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተከስቶ የነበረ ሲሆን ይህንኑ ለመቅረፍ ከዞንና ከወረዳ ማስተባበሪያ ማእከላት በመጠባበቂያ ከተያዘው ላይ እንዲሟላ ማድረጉን ቦርጉ አሳውቋል።
ህግ መተላለፍን በተመለከተ ደግሞ ቦርዱ ከሰዓታት በፊት ይፋ ያደረገውን የወላይታ ዞን ሶርቶ ቀበሌ ሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ ላይ የተፈፀመ የሕግ ጥሠትን ተከትሎ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ፓሊስ ኮሚሽን በላከው መረጃ በምርጫ ጣቢያው ላይ ተፈጸመ የተባለው የሕግ ጥሠት ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ለቦርዱ አሳውቋል።
በዚህም መሠረት የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ መስቀሌ ባሳን እና አቶ አበበ አይዛ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በፓሊስ ኮሚሽኑ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ተገልጿል።
በመሆኑም ቦርዱ በሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ የተቋረጠውን የድምፅ የመስጠት ሂደት እንዲቀጥል ወሥኗል።
በይርጋ ጨፌ ማስተባበሪያ ማእከል ስር በሚገኘው አዳሜ ምርጫ ጣቢያ ሱኬ ላይ የምርጫ ጣቢያው ሠራተኛ ወደ መራጮች የሚሥጥር ድምፅ መስጫ/መከለያ በመግባትና መራጮች ድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ ምልክት ሲያደርጉ ታይቷል።
በተመሳሳይ ጣቢያ ሌላ የጣቢያ ሰራተኛ የድምጽ መስጫ ወረቀትን መራጮች ወደ ሳጥን ከማስገባታቸው በፊት ተቀብላ ከፍታ ስታይ የተገኘች በመሆኑ በዐዋጁ የተደነገገውን የመራጮች በሚሥጥር ድምፅ የመስጠት መብትን ተላልፈው በመገኘታቸው በተፈፀመው የሕግ ጥሠት ላይ ቦርዱ በጣቢያው ሠራተኞችን ከስራ የማሰናበት ዕርምጃ መውሰዱን አሳውቋል።
በቀጣም ይህን ጣቢያ አስመልቶ ሌሎች እምጃዎች ሲኖሩ ቦርዱ የሚያሳውቅ መሆኑን ጠቁሟል።
በጋሞ ሰላም በር በዶሞኦ ቀበሌ በዶሞኦ ምርጫ ጣቢያ ወማለ 1 ላይ 17 መራጮች ከቀበሌ ደብዳቤ በማጻፍ ያለምንም የማንነት ማረጋገጫ ሊመርጡ የነበረ በመሆኑ እንዲሁም ከተመዘገቡበት ማንነት ጋር ያልተገናኘ የመታወቂያ ወረቀት እና የድምጽ መስጫ ካርድ ይዘው ወደ’ምርጫ ጣቢያ ለመምረጥ የመጡ ግለሰቦች ድምጽ እንዳይሰጡ መደረጉም ታውቋል።