የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ላይ በክልሎቹ የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ተገቢ የሆነ ምርመራ በማድረግ ለተጎጂዎች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ብሏል።
በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት በአካባቢው የተጠለሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች መጎዳታቸው አሳሳቢ መሆኑን አሳውቋል ኢሰመኮ፡፡
ኢሰመኮ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በባቢሌ አቅራቢያ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን የተኩስ ልውውጥ በተመለከተ ተጎጂዎችን፣ የየክልሎቹን የጸጥታ አካላትን፣ የቆሎጂ መጠለያ ሠራተኞችንና የሆስፒታል ባለሞያዎችን ማነጋገሩን አሳውቋል።
በአሁኑ ወቅት ግጭቱ የቆመ ቢሆንም፤ በተኩስ ልውውጡ ወቅት ቆሎጂ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ቢያንስ ስድስት ተፈናቃዮች ተገድለዋል፣ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል እንዲሁም በሌሎች የአካባቢው ሲቪል ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ስለዚህም ሁለቱ ክልሎች በቅንጅት በመሥራት በአካባቢው ለተከሰተው ግጭት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች ሰላማዊ መፍትሔ በመስጠት የነዋሪዎችንና የተፈናቃዮችን ደኅንነት በዘላቂነት የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠሩ ሲል ኢሰመኮ ሪፖርቱን አቅርቧል።
ለደረሰው ጉዳት ተጎጂዎች እንዲካሱና ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ባለማድረግ በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ባደረጉ የጸጥታ ኃይሎች አባላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እነደሚያስፈልግ ኢሰመኮ ገልጧል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተፈጠረው ግጭት ወቅት በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የነበረባቸው መሆኑን አሳውቀዋል።
ሰዎችበተለይም ቀድሞውኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ አስቸጋሪ ሕይወት ይመሩ የነበሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለሞትና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው አሳሳቢ ነው ሲሉ ምክትል ኮሚኝነሯ መግለጻቸውን ኢሰመኮ አመላክቷል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም ፤ በአፍሪካ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና እገዛን አስመልክቶ የተደረገው የአፍሪካ ሕብረት ስምምነት (ካምፓላ ስምምነት) መሠረት የመንግሥት የጸጥታ አካላት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የመጠለያ ጣቢያዎች ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ተግባራት ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።