በካይሮ በግብጻውያንና ኢትዮጵያውያን መካከል የተፈጠረው ግጭትና ሞት

በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በኢትዮጵያዊያንና እና በግብጻዊያን መካከል በተከሰተ ጸብ 1 ኢትዮጵያዊ ሲሞት ሌሎች 7 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ተወካይ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዓይን እማኝ ደግሞ የጸቡ መነሻ በግለሰቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት መሆኑን አስረድተዋል።

በግብጽ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ሰብሳቢ አቶ ጧሂር ኡመር በተፈጠረው ግጭት 1 ኢትዮጵያዊ ስደተኛ መሞቱን ገልጸዋል።

የፀቡ መነሻ ምን እንደሆነ ሲያስረዱም አንድ ባጃጅ የሚነዳ ግብጻዊ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሱቅ ባለቤት በር ላይ የነበረን ከሰል ረግጦ ሲያልፍ፤ ኢትዮጵያዊው ደግሞ ከሰሉን አበላሽተህ አድቅቀህብኛል ስለዚህ ክፈል በሚል እንደነበር አስረድተዋል።

የ2ቱ ግለሰቦች ግጭት ወደ ከፍተኛ ጸብ ሲሸጋገር በአካባቢው የነበረ ሌላ ኢትዮጵያዊ ወጣት ጸቡን ለመማብረድ መሐላቸው ይገባል።

በዚያን ጊዜ ግብፃዊው የባጃጅ ሾፌር ስለት አውጥቶ ደረቱን እንደወጋው በስፍራው የነበሩ አስረድተዋል።

የግብጻዊው ተባባሪዎች ወደአካባቢው ከመጡ በኋላ በስፍራው ከሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ከፈተኛ ግጭት ውስጥ መግባታቸውንና

ፖሊስም ጸቡን ለማብረድ ከኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት በማድረግና ተጠርጣሪውን በመያዝ ጥረት ማድረጉ ተገልጿል።

በስለት የተወጋው ወጣት ስደተኛ የመጀመሪያ ርዳታ የሚሰጡ ሃኪሞች ከቦታው ሲደርሱ ሕይወቱ አልፎ እንደቆየቻው እማኞች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ሰብሳቢው አቶ ጧሂር፤ በግጭቱ በ20ዎቹ አጋማሽ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ባለትዳርና የባጃጅ ሹፌር የነበረው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ መሞቱን ገልጾ፤ በካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ስለሁኔታው ያለው ነገር አልነበረም።

ሰኞ ዕለት በተከሰተው ግጭት ሰባት ኢትዮጵያውያን በስለት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ግብጻውያኑ ምን ያክል ጉዳት እነደደረሰባው አለመታወቁን እማኞች አስረድተዋል።

ግጭቱ በተፈጠረበት የካይሮው ማአዲ ስፍራ  በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ።  

ኢትዮጵያውያኑ በተፈጠረው ነገር ቁጣቸውን በአደባባይ ወጥተው የገለጹ ሲሆን፤  በኋላም ፖሊስ ጥቃት አድራሹን በመያዝና ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በመነጋገር ቁጣ እነዲበርድ አድርጓል።

የወጣቱ ኢትዮጵያዊ የቀብር ስነ-ስርዓት ካይሮ  በሚገኝ ኮዚካ የቀብር ስፍራ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት መፈጸሙ ታውቋል።

ግብጽ ውስጥ በባጃጅ ስራ በንግድና በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሉ። በቤት ሠራተኝነት፣ በምግብ ቤቶች፣ በመዝናኛና በግንባታ ስፍራዎች የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውም ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሱዳን ጉዳይ በመከረው ጉባኤ ላይ ትናንትና በግብጽ ተሳትፈው መመለሳቸው ይታወሳል። በግብጽ ካይሮ ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታሕ ኤልሲሲ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ትብብር በሰፈነበት መንፈስ ውይይቶች ማድረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

netevm.com