በ5 ከተሞች የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ከተሞች የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ጀምሯል።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ምክንያት አድርጎ ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነትና ፍትሕ ለሁሉም በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን የዘንድሮውን ፌስቲቫል አምስት ከተሞችን እንደሚያዳርስ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ አስታውቋል።

በፌስቲቫሉ ሰብአዊ መብቶችን ማዕከል ያደረጉ አዳዲስ እና ከዚህ በፊት ለዕይታ የቀረቡ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ተቀባይነትን ያተረፉ የሙሉ ጊዜ እና አጫጭር ፊልሞች እንዲሁም ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ፡

በአምስቱ ከተሞች የሚካሄደው ሁለተኛው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዕቅድ መሰረት

 በአዳማ- ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በኦሊያድ ሲኒማ ይካሄዳል

 በአዲስ አበባ- ታኅሣሥ አንድ የተጀመረው ፌስቲቫል በታኅሣሥ18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ ይካሄዳል ።

በባሕር ዳር- ታኅሣሥ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል፣ በሃዋሳ- ታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሌዊ ሲኒማ እንዲሁም፣  በጅግጅጋ- ታኅሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በኤምሲኤም ሆቴል የሚካሄድ መሆኑን ኢሰመኮ አስታውቋል።

15 ፊልሞች ለእይታ የተሰናዱበትና በመዓዛ ወርቁ ፊልም ፕሮዳክሽንስ አስተባባሪነት የሚዘጋጀው ፌስቲቫሉ በሴቶችና ሕፃናት መብቶች፣ በስደተኞች፣ ፍልሰተኞች እና በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች፤ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ላይ እንደሚያተኩር ተውቋል።

በተጨማሪ በፍትሐዊ እና ሰብአዊ የሥራ ክፍፍል፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እና ጥቃት፣ እንዲሁም በማረሚያ ቤት የወጣት ጥፋተኞች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች ተካተውበታል፡፡

ፊልሞቹ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ እና ሲዳምኛ ቋንቋዎች የተሠሩ ወይም አጋዥ ጽሑፍ ያላቸው መሆናቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።

ፌስቲቫሉን በይፋ ለማስጀመር በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በሀገራችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አሁን ላለበት አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ለመድረሱ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ስለ ሰብአዊ መብቶች ያለው አነስተኛ ግንዛቤ በአሉታዊ መልኩ አስተዋዖ አድርጓል ብለዋል።

ኢሰመኮ በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱ ከለያቸው ቁልፍ የውጤት መስኮች መካከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እንዲኖር ማስቻል ሲሆን የኪነጥበብ ዘርፉ የሰብአዊ መብቶችን ግንዛቤ ከማስፋፋት እና ከማስተማር አኳያ ከፍያለ ሚና ይጫወታል።

ይህ የሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ የፊልም ፌስቲቫል በሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት፣ ለመመማማር እና በሰብአዊ መብቶ መርሆች የታነጸ ትውልድን ለመቅረጽ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው በፊልም እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ተማሪዎች እና ሌሎች ተመልካቾች ይታደሙበታል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ የተጀመረው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ ከኅዳር 28 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ፣ በአዲስ አበባ እና በሃዋሳ ከተሞች መካሄዱ ይታወሳል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.