የክብር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ ብዙዎችበጥዑመ ዜማዎቹ ሲያስታውሱት ይኖራሉ።
ባለፉት ስልሳ ዓመታት በኢትዮጵያ የጥበብ ሰማይ ለይ ነግሶ የትውልድ ተምሳሌት ሆኖ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ ወሳኝ ድርሻ ከተጫወቱ ድንቅና አንጋፋ የጥበብ በለሙያዎች አንዱ የሆነው ታላቁ አርቲስት የክብር ዶ/ር አሊ ብራ ከአባቱ አቶ መሐመድ ሙሣ እና ከእናቱ ወ/ሮ ፋጡማ አሊ በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ ሠፈር ተወለደ።
የልጅነት መጠሪያ ስሙ አሊ መሐመድ ሙሣ የሆነውና አሊ ብራ በሚል የጥበብ ስሙ የሚታወቀው እና በቅርብ ወዳጆቹ Adeeroo (አጎት) በሚል የፍቅርና የክብር ስም የሚጠራው ይህ የጥበብ ስው በህፃንነቱ የአረብኛ እና የቁርአን ትምህርት ሲማር ቆይቶ እስከ አምስተኛ ክፍል መድረሳ ጀዲዳ በሚባለው ትምህርት ቤት፣ መደበኛ ትምህርቱን ተከታተለ።
ከዚያም ልኡል መኮንን ትምህርት ቤት በሚባለው ትምህርት ቤት ትምህርቱን የቀጠለ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በካቴድራል ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል። ከአገር ውጪም አሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ሳንታ ሞኒካ ከሌጅ የሙዚቃ ትምህርት በመከታተል የጥበብ ዕውቀትና ክህሎቱን አሳድጎ በላቀ የሙያ ብቃት ሕዝብን ለማገልገል ያለውን ፍላጎት በተግባር አረጋግጧል።
አርቲስት አሊ ቢራ አባት ልጃቸው አድጐ መካኒክ እንዲሆንላቸው ይመኙ የነበረ ቢሆንም አርቲስት አሊ ቢራ በልጅነቱ ዝንባሌው ስፓርት እና ሙዚቃን መውደድና ሲኒማ መመልከትን ማዘውተር ነበር።
በልጅነቱ ያደረበትን የሙዚቃ ፍላጐት ለማርካትና የሕይወት ጥሪው የነበረውን ትክክለኛ ጉዞ ለመጀመር በ1954 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የኦሮሞ ባህልና ጥበብ ማሳደግን ዓላማው አድርጎ የተቀስቀስው የአፍረን ቀሎ እንቅስቃሴ ውጤት የሆነውና በተለምዶ አፍረን ቀሎ ባንድ የሚባለው ኡርጂ በከልቻ ባንድ መቋቋም ወጣቱ አሊ ልዩ አጋጣሚ ፈጠረለት።
በወቅቱ የኡርጂ በከልቻ ባንድ አንጋፋ ሙዚቀኞችን ይዞ በሥሩ ህሪያ ጃለላ የተባለ የታዳጊ አርቲስቶች የሙዚቃ ቡድን ስለነበረው።
ወጣቱ አሊ መሐመድ ሙሳም ህሪያ ጃለላ (የፍቅር ጓዳኞች) ባንድ አባል በመሆን የህይወት ጥሪው ወደነበረውና መላ እድሜውን ወዳሳለፈበት የሙዚቃ አንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ጀመረ።
በ13 ዓመቱ በድምፃዊነት ሥራውን እንደ ጀመረ የዋናው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን ማለትም ኡርጂ በከልቻ ባንድ ባዘጋጀው አንድ የበዓል ዝግጅት ላይ Birraadhaa barihee ililliin urgooftee የተባለ የመጀመሪያ ዘፈኑን ለህዝብ በማቅረብ የድምፅና የአዘፋፈን ልዩ ብቃቱን በአደባባይ አስመሰከረ።
የብራ ወቅት መጣ፣ አበባው አወደ የሚል ጥሬ ትረጉም ያለው ይህ የአርቲስት አሊ ቢራ የመጀመሪያው ዘፈን በርግጥም በአሮሞ የዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን እና ለአፋን ኦሮሞ ዘመናዊ ሙዚቃ ብሩህ ዘመን እየመጣ መሆኑን ያበሠረ እንዲሁም በኦሮሞና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ውስጥ ልዩ ታሪክ የሚሠራ ታላቅ የሙዚቃ ንጉስ መወለዱን ያበሠረ ልዩ ዘፈን ሆኖ በታሪክ ተመዘገበ።
አሊ መሐመድ ሙሣም አሊ ቢራ በተባለ የጥበብ ንግስና ስሙ መጠራት ጀመረ። አንጋፋነቱንም ከታላላቆቹ ተረክቦ በጥበብ አድማስ ላይ በልጅነቱ አንደ ነገሠ፣ እንደ ተወደደ እና እንደ ተከበረ ሙሉ እድሜውን የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ምርጥ የጥበብ ሰው በመሆን አገለገለ።
ይህ ባለ ብዙ ተስጥኦ የጥበብ ስው ከሂሪያ ጀለላ ባንድ ወደ ዋናው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን ማለትም ወደ ኡርጂ በከልቻ ባንድ አድጐ ከታላላቆቹ የሙዚቃ በለሞያዎች ከእነ የክብር ዶ/ር አሊ ሸቦ እና ጉደኞቹ ጐን ተሰልፎ በየመድረኩ ቀርቦ በመዝፈን በድማፃዊነት ሕዝብ ማገልገለን ቀጠለ።
በግል ጥረቱ ሊድና ቤዝ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኦርጋን፣ አኮርዲዮ፣ ኡድ እና የመሳስሉትን የሙዚቃ መሣሪያዎች በመማር የራሱን ዜማዎች እየደረሰ መዝፈንና ጓደኞቹንም በሙዚቃ በማጀብ ድንቅ አርቲስት ሆኖ ቀጠለ። በዚህም የአፋን አሮሞ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክን ቀየረ።
የአሮሞ ዘመናዊ ሙዚቃን መሠረት ጥሎ ገንብቶና አሳድጐ ለታለቃ ደረጀ በማብቃት የዘመናዊ የአሮሞና የመላ ኢትዮጵያ የጥበብ መሐንዲስ ለመሆን በቃ። የሙዚቃ ንግስናውንም በላቀ ደረጃ አረጋገጠ።የድሬዳዋ ከተማም የኦሮሞ የዘመናዊ ሙዚቃ ማዕከል ሆነች።
የክብር ዶ/ር አሊ ቢራ ከጓደኞቹ ጋር በየአካባቢው እየዞረ የሙዚቃ ሥራዎቹን በማቅረብ በአጭር ጊዜ እጅግ ታዋቂና ተወዳጅ አርቲስት ሆኖ እያገለገለ አመታትን አስቆጠረ።
ከዚህ በኋላ በኦሮሞ ሙዚቃ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የሙዚቃ ትርኢት በውጪ አገር ማለትም በጂቡቲ ለማቅረብ ለኡርጂ በከልቻ ባንድ በመጣው ግብዣ መሠረት ከጓደኞቹ ጋር ወደ ጂቡቲ ያደረጉት ጉዞ ለእሱም ለጓደኞቹም ከባድ ችግርን አስከተለ።
ጂቡቲ ሄደው ሙዚቃ ለመጫወት ፍቃድ ጠይቀው በመከልከላቸው ያለ መንግሥት ፍቃድ ወደ ጂቡቲ ጉዞ አደረጉ።
ምንም እንኳ ከሕዝብ ጋር ተገናኝተው የሙዚቃ ሥራቸውን ማቅረብ የቻሉበት አጋጣሚ ቢሆንም አርቲስት አሊ ቢራ በጅቡቲ ድንበር ለአንድ ወር ታሠረ። ወደአገር ቤት ሲመለሱም እሥራት ሸልማታቸው ሆነ።
በወቅቱ የአሊ ቢራ ጠያቂ ሕዝብ የድሬዳዋ እሥር ቤትን በማጨናነቁ ወጣቱ አርቲስት አሊ ቢራ ወደ ሐረር ተወስዶ ለረጅም ጊዜ ታሠረ። የሙዚቃ ባንዱም በተፅዕኖ ተበታተነ።
በመሆኑም ይህ ታላቅ አርቲስት ሕይወቱን ለመታደግና የሙዚቃ ፍቅሩንም ለማርካት ድሬዳዋን ለቅቆ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ በዚያውም በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ከታላላቆቹ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ከእነ ጥላሁን ገሠሠ ፤መሐሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ እና ከመሳስሉት ጋር ለሶስት አመት አገለገለ።
ከዚያ በኋላ በወቅቱ በነበረው አንዳንድ ተፅዕኖ በመከፋት ለዘልዓለሙ ከሙዚቃ ዓለም ለመሰናበት ወስኖ እሱን በሚያዉቁ የምድር ባቡር ኩባንያ ኃላፊዎች አማካይነት ወደ አዋሽ ከተማ ሄዶ የምድር ባቡር ጣቢያ የውሃ መካኒክ በመሆን ለማገልገል ተገደደ።
ይሁን እንጂ ለጥበብ በመፈጠሩና በሙዚቃ አለም ውስጥ ሆኖ ሕዝብን ማገልገል የአርባ ቀን ዕድሉ በመሆኑ ከተወሰኑ አመታት ቆይታ በኋላ ውሳኔውን ቀይሮ ወደ ሙዚቃው ተመልሶ ፊንፊኔ ውስጥ ሥራውን ቀጠለ።
በፊንፊኔም የመጀመሪያው የኦሮሞ ዘመናዊ የሙዚቃ ባንድ የሆነውን አዱ ብራ ባንድ በመመሥረት በሙኒክ ክለብ፣ በዛምቤዚክ ክለብ እና በመሳሰሉት የምሽት ከለቦች፣ ሲሠራ ቆየ።
በኋላም ባንዱን ለጓደኞቹ ትቶ በአገሪቱ ታላላቅ የሙዚቃ ቡድኖች ማለትም በአይቤክስ ባንድ፣ በኢትዮ ስታር ባንድና በመሳሰሉት የሙዚቃ ቡድኖች ውስጥ በዲአፍሪቅ ሆቴል፣ በራስ ሆቴል፤ በሐራምቤ ሆቴል፣ በሂልተን ሆቴል እና በመሳሰሉት ዉስጥ በድምፃዊነት ከተላላቆቹ የአገሪቱ ድምፃውያን ጋር በምሸት ከለብ በመሠራት ልዩና አቻ የሌለው የጥበብ ባለሞያነቱን አስመስከረ።
ከሁሉ በላይ በሥራውና በፀባዩ፣በሰው ወዳድነቱና በሰዉ አክባሪነቱ እጅግ መወደድን የታደለው አርቲስት አሊ ቢራ የሙዚቃ ሥራዎቹን አሳትሞ ለህዝበ በማቅረብም የኦሮሞ ሙዚቃ በአገራችን የሙዚቃ ገበያ ውስጥ ተገቢ ሥፍራ እንዲያገኝ አስችሏል። ከዚህም በላይ በተለያዩ የብሔር ብሔር ብሔረስቦች ቋንቋዎች በመዝፈን ለኦሮሞ ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የሀገራችን የሙዚቃ እድገት መሠረት የሆኑ ሥራዎችን አበርክቷል። ምርጥ ድምፃዊ ለመሆንም በቅቷል።
አርቲስት አሊ ቢራ በአገራችንም ሆነ በአፍሪካ ልዩ የሚያዳርጉት በርካታ ተስጥኦዎችና ሥራዎች ያሉት እጅግ የሚደነቅ ድምፃዊ ነው። ሰባት ቋንቋዎችን ይናገራል። በስድስት ቋንቋዎች ማለትም በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማልኛ፣ በሐረሪ፣ በአማርኛ፣ በአረብኛ እና በስዊዲሽ ቋንቋዎች ዘፍኗል።
አስደናቂ የዜማ ደራሲ እና ሙዚቃ አቀናባሪ ነው። በዚህ መልክ ተስረቅራቂ ድምፅ ያለው ድምፃዊ፣ የበርካታ የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተጫዋች፣ ሙዚቃ አቀናባሪና በስድስት ቋንቋዎች የዘፈነ ምናልባት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ምናልባትም ብቸኛው አፍሪካዊ ሊሆን ይችላል።
ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለጓዳኞቹ ለአርቲስት ጥለሁን ገሠሠ እና አርቲስት መሐሙድ አህመድ ጭምር ዜማዎችን ደርሷል። በአገራችን ከፍተኛ የድምፅ ቅላፄ ካላቸው ባለልዩ ተሰጥኦ ምርጥ ድምፃውያን አንዱ ነው። ለአፔራ አዘፋፈን የሚመች ኦፕራ ድምፅ አለው። መድረክ ላይ ቆሞ ሲዘፍን ሰዉን በፍቅር የመስብ ኃይል አለዉ (Magnetic attraction)አለዉ።
በአጠቃለይ የክብር ዶ/ር አሊቢራ በሕይወት ዘመኑ 267 ምርጥ ዘፈኖችን ዘፍኗል። ዘፈኖቹ በሙሉ በሁሉም የሚወደዱ፣ ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ነው የሚባለውን አባባል በተግባር ያሳየ፣ የአገራችን ወጣት ድምፃውያን ወደ ሙያዉ ሲገቡ ሙያቸውን ለማዳበር ከሁሉ በላይ የሚመርጡት፣በትንሽ በትልቁ የሚወደዱ በየትኛውም የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የሚዘፈኑ ምርጥ ዘፈኖች ናቸው።
ሥራዎቹ ተሰምተው የማይጠገቡ፣ ቋንቋውን ለሚችል ብቻ ላይሆን ሙዚቃን ለሚወድ ሁሉ የሚሰማሙ የማያረጁና የማይረሱ፣ ከትውልድ ወደ ትወልድ የሚተላለፉ ዘመን ተሻጋሪ የአገር ቅርሶች ናቸው።
አርቲስት አሊ ቢራ ያልዘፈነበት የሕይወት ጉዳይ የለም። ፍቅርን፣ እርቅን፣ ሰላምና መተሳስብን አጉልቶ አሳይቷል። አንድነትን ሰብኳል።
በአገራችን ፖለቲካ ልዩነትና በተለያዩ መንገዶች መከፋፈልና መናቆር እያቆጠቆጠ በመጣበት በ1960ዎቹ አካባቢ Haati teenya Takkaa Maaltu addaan nu baasee? እናታችን አንድ ነች ምንድነው የሚያለያየን የሚል ብርቱ ጥያቄን በዘፈን በማንሳት መቻቻልና ተቀራርቦ ችግርን በውይይት መፍታትን፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚሰብክ ጥልቅ መልእክት ያለው ዜማ በማቀንቀን ፈር ቀዳጅ የህዝቦች የአንድነት ድምፅ ሆኖ አገልግሏል።
የአሊ ቢራ ድምፅ የፍቅርና የነፃነት ድምፅ ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ እና ለመላ ጭቁኖች መብት፣ ነፃነትና አኩልነት ጠበቃ ሆኖ የዘመረ፣ የቀሰቀስና ሕዝብን ያንቀሳቀስ ወደር የሌለው ጀግና የሕዝብ ልጅ እና ግንባር ቀደም የነፃነት አርበኛ ነው።
በዚህ ሥራውም ተወዳዳሪ የሌለው የመብት ተሟጓች በመሆን በኦሮሞና በኢትዮጵያ ብሔሮች ልብ ውስጥ ሁሌም ሲታወስ፣ ሲወደስና ሲዘከር የሚኖር የሕዝብ ባለውለታ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡ በዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ የሁሉንም ቀልብ የሚስብ ተፅዕኖ ፈጣሪ የትውልድ ተምሳሌት ለመሆንም በቅቷል፡፡
በአጠቃላዩ ዶ/ር አሊ ቢራ በኦሮሞና በመላ ኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገት ላይ ደማቅ አሻራ ያኖረ እና በቀላሉ የማይተካ የዘመን ክስተት ነው።
የክብር ዶ/ር አሊ ቢራ በድንቅ የጥበብ ስራው በቀድሞው መንግሥት ባለመወደዱ በርካታ እንግልት፣ እሥራትና ችግር ደርሶበታል። ይህ አሳሳቢ ሁኔታ እየከፋ በሄደበት በ1977 ዓ.ም የስዊድን ዜጋና በኢትዮጵያ የአገሯ ዲፕሎማት ከነበረችው የቀድሞ ባለቤቱ ወ/ሮ ብርጊታ አስትሮም ጋር አገሩን ጥሎ ወደ ስዊድን ለመሰደድ ተገደደ።ለተወሰኑ አመታት ስዊድን፣ ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ ኖሯል።
ከባለቤቱ ከተለያየ በኋላም ካናዳን የረጅም ጊዜ የመኖሪያ አድራሻው አድርጎ ነበር። በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራልያና በመካከለኛው ምሥራቅ በመዘዋወር የአገራችንና የሕዝቦቿ የጥበብ አምባሳደር በመሆን አገልግሏል። በታላላቅ የአለም መድረኮች ላይ ሰርቷል።
ኢትዮጵያውን የዲያስፓራ አባላትን በማዝናናት እና በአይነ ህሊናቸው አገራቸውን እንዲያዩና ናፍቆታቸውን በሙዚቃ እንዲወጡ በማድረግ ታላቅ ውለታ ውሏል።
ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ አሊ ቢራ የህፃናት ትምህርት ፈንድ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በማቋቋም ወገኑን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡
አርቲስት አሊ ቢራ በፀባዩ ሰዉ ወዳድ፣ ትንሽ ትልቁን አክባሪ፣ ቸር እና ለተቸገረ መስጠትና ለህዝብ መስጠትን የታደለ፣ በቀልድ እያዋዛ የማዝናናት ልዩ ተስጥኦ ያለው ሁለገብ የጥበብ ሰው ነዉ።ከልጅነቱ ጀምሮ በዘፋኝነቱና በነፃነት ታጋይነቱ እንደተወደዳ እና እንዳተከበረ የዘለቀው ታላቁ የሙዚቃ ንጉስ የክብር ዶ/ር አሊ ቢራ ምጥቀት ላለው የሙዚቃ ሥራው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሸልማቶችን ከአገር ዉስጥና ከውጭ አገራት አግኝቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው ከ100 በላይ ሸልማቶችንም ወስዷል። ምርጥ የአፍሪካ ዘፋኝ ሆኖ ያገኘዉ ሸልማትም ከእነዚሁ ውስጥ ይገኛል።
ከአገር ውስጥም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሽልማት ተሸልሟል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የላቀ አገልግሎት ላበረከቱ የሕዝብ ባለውለታዎች የሚሰጠውን ታላቅ የክብር ኒሻን፣ መኖሪያ ቤትና ቪ8 መኪና የሸለመው ሲሆን የጅማና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎችም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክተውለታል፡፡
ከዚህም ባሻገር የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በስሙ ሰይሟል። አዳማ ከተማ ውስጥ መንገድ፣ ድሬዳዋ ውስጥ ደግሞ ፓርክ በስሙ ተሰይሞለታል። ከተለያዩ የጥበብ ሽልማት አዘጋጅ ድርጅቶች የእድሜ ልክ የላቀ አገልግሎት ሽልማቶችን ተቀብሏል።
ታላቁ የሙዚቃ ንጉስና የኦሮሞና የአራችን የሙዚቃ አባት የሆነው አርቲስት አሊ ቢራ ከአብራኩ የወጡ ልጆች ባይኖሩትም የትውልድ ተምሳሌት በመሆን በርካታ ዕውቅ አርቲስቶችን አፍርቷል። በምርጥ የሙዚቃ ሥራዎቹ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ አስቀምጧል።
በኦሮሞ የሞጋሳ ሥርዓት እልሊ ቢራ ተብላ ተሰይማ አሮሞነትን የተቀዳደችው እና እየተንከባከበች አብራ ከምትምኖረው ባለቤቱ ወ/ሮ ሊሊ ማርቆስ ጋር በተወለደበትና ከፍተኛ የህዝብ ፍቅር ባገኘበት አገሩ በሰላምና በፍቅር እየኖረ በተደጋጋሚ ያጋጠመውን የጤና ችግር በውጪ አገርና በአገር ውስጥ እየተከታተለ ወገኑን በሙያዉ እያገለገለ ሰንብቷል።
በመጦሪያ ወቅቱ ከፍተኛ ህመም አጋጥሞት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 27 ቀን ምሽት በተወለደ በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። አገራችን ኢትዮጵያም ታላቁና ተወዳጅ ልጇን አጥታለች።
ታላቅ ስራ ሰርቶ በሕዝብ ልብ ውስጥ የትዝታ ቤቱን ገንብቶ ያለፈ በመሆኑ ስሙና ስራው ህያው ሆኖ ይኖራል
ከአንጋፋው የኪነጥበብ ሠው የተወሰኑ ሥራዎችን እንገባበዝ። የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ያልሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአሊ ቢራ ዘፈኖች ጋር አብረው ያንጎራጉራሉ። በትዝታ ይነጉዳሉ። ይነሸጣሉ።
ምንም እንኳ የዘፈኑን ያህል ባይሆንም “Nin’deemaa/ኒን ዴማ” የሚለውን ዘፈን ከአመታት በፊት ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ነበር።
Nin'deemaa! /ኒን ዴማ!
Nin’deemaa Nin’deemaa, biyya feteen daqaa(X2)
gaara feteen bahaa, laga feteen cehaa
Deebi’ee arguudhaaf, ija kee bareedaaSiwajjiin dabarsuuf, jiru tiyya hundaa(2)
ሄዳለሁ ሄዳለሁ፣ ካልሽኝ እሄዳለሁ (X2)
ተራራ እወጣለሁ፣ ወንዝ እሻገራለሁ
ዳግመኛ ለማየት፣ የሚያምር አይንሽንካንቺ ጋር ላሳልፍ፤ የሕይወት ዘመኔን(X2)
Aduun seentee baatuus, waanuma keen Yaadaa(X2)
Urjii ji’a arguus, Jaalala keen dhaadaaBonaafi ganni, arfaasaafi birraa
Yaadannoo naafidan, jaalala keetirraa(X2)
ፀሃይ ጠልቃ ወጥታ፣ አንቺኑ አስባለሁ(X2)
ኮከብ ጨረቃም ሳይ፣ ፍቅርን ቃትታለሁበጋና ክረምቱ፣ በልግና ፀደይ
ትዝታ አመጡልኝ፣ ካንቺው ፍቅር ላይ
Natti himii yaa’lattu, kee garaan maal yaadaa(X2)
Osso wal-jaalannu, maaf jiraannaa addaa?Jabaadhu hiriyaakoo, obsaan haajiraanu
Amantiif jaalalaan, abdiin haa’eeganu(X2)
ንገሪኝ ውድዬ፣ ሆድሽ ምን ያስባል
እየተዋደድን፣ እንዴት ብቻ ይኖራል?አይዞሽ የእኔ ፍቅር፣ በትዕግስት እንኑር
በተስፋ እንጠብቅ፣ በእምነትና በፍቅር (X2)
Nin deemaa Nindeemaa, biyya feteen daqaa(X2)
gaara feteen baha, laga feteen ceehaa
Deebi’ee argudhaaf ija kee baredaaSiwajjiin dabarsuuf, jiru tiyya hundaa(2)
ሄዳለሁ ሄዳለሁ፣ ካልሽኝ እሄዳለሁ (X2)
ተራራ እወጣለሁ፣ ወንዝ እሻገራለሁ
ዳግመኛ ለማየት፣ የሚያምር አይንሽንካንቺ ጋር ላሳልፍ፣ በሙሉ ህይወቴን(X2)
ነብስ ይማር የክብር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ።
የጥንቅር ምንጮች (ኢቢሲ፣ ፋና፣ ሚውዚክ ዴይ፣ የድሬዳዋ ሙዚየም፣ የአርቲስቱ አድናቂዎች)