የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከዘርፈ ብዙ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ እና እንዳይባባሱ የተለያዩ የምክር፣ የሽምግልና እንዲሁም የውትወታ ተግባራት እንደሚያከናውኑ አስታውሰዋል።
“የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት መሠረት በማድረግ፣ የኃይማኖቶችና ሌሎችም ነጻ ተቋሞችን ነጻነት ማክበርና መጠበቅ አስፈላጊነት በማጤን፣ ሁሉም ሰው እና ማኅበረሰብ፣ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ” ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሦስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት “የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ቤተ ክህነት” ተብሎ የሚጠራ አዲስ ቤተ ክህነት ማቋቋማቸውን ኢሰመኮ አስታውሷል ኢሰመኮ አስታውሷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ሹመቱን ውድቅ በማድረግ ሦስቱን ጳጳሳት ጨምሮ እነሱ የሾሟቸውን የሃያ ስድስት አባቶችን ማዕረግ በማንሳት ከቤተክርስቲያኗ በውግዘት እንዲገለሉ መወሰኑ ይታወሳል ብሏል ኢሰመኮ በመግለጻው።
ይህንን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠሩ ያሉ ክስተቶች እና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርበት በመከታተል፣ እንዲሁም ሁሉንም ወገኖች እና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ለችግሩ እልባት ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አሳውቋል።
ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ ባደረገው ክትትልና ምርመራ አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁት ጳጳሳት በአንዳንድ ቦታዎች በኃላፊዎች ድጋፍ ጭምር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን መያዛቸውን ገልጿል።
ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ለመያዝ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ እርምጃውን ለመቃወም የወጡ ሰዎችን ለመበተን በመንግሥት ጸጥታ አባላት በተወሰደ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ እና ከጸጥታ አባሎቹ ጋር ሲተባበሩ በነበሩ ሰዎች ቢያንስ ስምንት ሰዎች በጥይትና በድብደባ መገደላቻውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል።
በተጨማሪ ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ለተለያየ ዓይነትና መጠን የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም በርካታ ሰዎች ለተለያየ ጊዜ መጠን መታሰራቸውን አሳውቆ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በሻሸመኔ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 13 መሆኑን ለኮሚሽኑ የገለጹ በመሆኑ የማጣራት ሂደቱ መቀጠሉን ይፋ አድርጓል።
በተለያዩ ቦታዎች አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁትን ጳጳሳት በተቃወሙ ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጭ እስራት እንደተፈጸመ፤ እንዲሁም ሲኖዶሱ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚታሰበውን የጾም ወቅት አስመልክቶ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ በተለያዩ ቦታዎች እስር፣ ወከባ፣ ከሥራ ቦታና አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ማግለል እንደተፈጸመ አሰመኮ ገልጿል።
የችግሩ ግዝፈት ቢለያይም በተለይ በነቀምቴ፣ በግምቢ፣ በደምቢ ዶሎ፣ በሻምቡ፣ በአሰላ፣ በሻሸመኔ፣ በጭሮ፣ በያቤሎ፣ በጅማ፣ በቡሌ ሆራ፣ እና በነጌሌ ቦረና ከተሞች ከሕግ ውጭ እስራትና ተመሳሳይ የማዋከብ ድርጊቶች እንደተፈጸመ ታውቋል፡፡
በመንግሥት የጸጥታ አባሎች ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል አጠቃቀም በጥይት እና በድብደባ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ እስሮችና የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ እንዲሁም ሲኖዶሱ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ እስሮች፣ ከአገልግሎት እና ከሥራ ቦታ ማግለልና ማንገላታት ፍጹም ተገቢ ያልሆኑ እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ በነጻነት ሃይማኖታቸውን እና ሐሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚፃረሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መሆናቸውን አሰመኮ ጠቁሟል።
ስለሆነም መንግሥት የተሟላና ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ እና የተጎዱትንም ሊክስ ይገባል። በተጨማሪም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ኃይል ከመጠቀም፣ ከማንገላታት፣ ከሕገ ወጥ እስር እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ያለበቂ ምክንያት ከመገደብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ብሏል ኢሰመኮ፡፡
በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎችም መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሥጋቱን የሚጨምሩ በመሆናቸው በሁሉም አካላት ኃላፊነት የተሞላው የሚዲያ አጠቃቀም እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
እየተከሰተ ያለው ችግር አስቸኳይ እልባት ካላገኘ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሥጋት ነው ያለው ኢሰመኮ፤ ስለሆነም ኮሚሽኑ ከመደበኛው የክትትል እና የምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በሙሉ በማነጋገር እና በመመካከር፣ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረው ችግር የሃይማኖት ነጻነት መሠረታዊ መብትና የሃይማኖት ጥበቃ ሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት በቤተ ክርስቲያኗ የውስጥ ሥርዓት መሠረት እንዲፈታ ሃሳብ አቅርቧል።
የመንግሥት ሰላምና ጸጥታ የማስከበር ተግባርና ኃላፊነት በሕጋዊ ሥርዓት እንዲመራ፣ ሰብአዊ መብቶች በሁሉም ወገኖች እንዲከበሩና እንዲረጋገጡ የሚያስችል የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን ኢሰመኮ በመግለጫው አመላክቷል።