ኢሰመኮ የፓርቲዎችን የመሰብሰብ መብት መከልከል ተቃወመ

EHRC
Human rights commission report on Addis Ababa Schools

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ በእናት ፓርቲ እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የመሰብሰብ መብት መከልከል እንዲሁም የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ በፓርቲው አስተባባሪዎች ላይ ስለደረሰው እንግልትና እስራት ሲከታተል መቆየቱን አስታውሷል።

ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ማነጋገሩን ገልጾ

  • እናት ፓርቲ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ሊያካሂደው የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ስብሰባ እንዲሁም ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በጋምቤላ ሆቴል ውስጥ ሊያካሂድ የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ስብሰባ እንዳይካሄድ መስተጓጎሉን ኢሰመኮ አሳውቋል።  
  • ለፓርቲዎቹ ስብሰባ ተዘጋጅተው የነበሩ ቦታዎች ጥበቃዎችና ሠራተኞች ማንነቱ ተለይቶ ካልታወቀ የበላይ አካል ተሰጥቷል ባሉት ትዕዛዝ መሠረት ስብሰባዎቹን መከልከላቸው እና ስብሰባዎቹ ሊካሄድባቸው በነበሩበት አካባቢዎች የደንብ ልብስ በለበሱ የፖሊስ አባላት እና ሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታና ደኅንነት አባላት ስብሰባው እንዲካሄድ ከማገዝና ከማሳለጥ ይልቅ የማደናቀፍ ተግባር መከናወኑን ገልጿል።   
  • የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ የፓርቲ አስተባባሪዎች ላይ እስራት እና እንግልት የተፈጸመ መሆኑን ኢሰመኮ ጠቁሟል፡፡  

ኢሰመኮ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ክትትሎች ሌሎች ተፎካካሪ/ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ለምሳሌ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፖለቲካ ፓርቲ እና የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በተለይም የአመራር አባሎች ላይ የተደረገውንም ገደብ፣ ማዋከብ እና እስራት መኖሩን አስታውሷል፡፡ 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ መብት እና የሰዎችን በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸውን የሚገድቡ ተግባሮችን የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግሥት ነው” ብለዋል።  

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔዎቻቸውንም ሆነ ሌሎች የድርጅቶቻቸውን ስብሰባዎች እንዳያደርጉ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት የሚደረጉ ወከባዎች፣ ክልከላዎችና እገዳዎች የሕግ እና የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና የመሳተፍ መብቶች ጥሰቶች ናቸው ብሏል ኢሰመኮ።   

ማንኛውም ሰው የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነጻነት አለው ያለው ኢሰመኮ፤ ሰብአዊ መብቶች በሁሉም ጊዜ ለሁሉም ሰዎች እኩል መከበር፣ መጠበቅ እና መሟላት ያለባቸው ቢሆንም አንዳንድ መብቶች ከሌሎች በተለየ በዴሞክራሲና ሕዝባዊ ተሳትፎዎች ውስጥ ሂደቱን አሳታፊ፣ ነጻና ፍትሐዊ ከማድረግና ዴሞክራሲያዊ የሆነሥርዓት ከመገንባት አንጻር አስፈላጊነታቸው ጎልቶ ይወጣል ብሏል።

የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ዜጎች በመረጡት የፖለቲካ አመለካከት ለመደራጀት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት እና በሕዝብ ጉዳዮች ውስጥ ለመሳተፍ አስፈላጊ ናቸው፡፡ በመሆኑም የመሰብሰብ መብት በተለይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አስፈላጊ ነው ሲል ኢሰመኮ አብራርቷል።  

መንግሥት ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማመቻቸት እና ለተሳታፊዎች ጥበቃ እና ከለላ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

ከመንግሥትም ሆነ ከሦስተኛ ወገን የሚመጡ ማስፈራራቶች እና ዛቻዎች እንዲሁም ማጉላላቶችን በመከላከል እና እነዚህ ጣልቃ ገብነቶች በአግባቡ በማጣራት እና ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን የማስፈን ግዴታ አለበት ብሏል፡፡

ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ክልከላዎችን በመጠቀም ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን ከመጠቀም እንዲያፈገፍጉ ከማድረግ በመቆጠብ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ከመንግሥት የሚጠበቅ ግዴታ ነው ሲል ኢሰመኮ አሳስቧል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.