የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሠራር ሰብአዊ መብቶችን ሊያከብር እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሠራር ከሕግ ያፈነገጠ መሆኑን ገልጿል።

የተሟላ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ ወይም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ እንዲሻሻል ያስፈልጋል::

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሠራተኞች ላይ የተሠሩ ጥናቶችን እና የቀረቡለትን በርካታ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ባለ 58 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠሩ በተለይም በሃዋሳ፣ ባሕር ዳር፣ አዲስ አበባ እና ጅማ ከተሞች መረጃዎች መሰብሰቡን ያሳወቀው ኢሰመኮ በግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መብቶች አተገባበር ላይ ከፍተኛ ችግር መገኘቱን ገልጿል።

በተለይም በኤጀንሲዎቹ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ለሚሠሩት ሥራ በቂ ክፍያ የማያገኙ በመሆናቸው፤ በተለያዩ ሕጎች እውቅና ያገኘው በቂ ክፍያ የማግኘት መብታቸው እየተከበረላቸው እንዳልሆነ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ ተጠቃሚ ድርጅቶች በቀጥታ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች እና በተመሳሳይ መደብና ቦታ በኤጀንሲዎች አማካኝነት ተቀጥረው በሚሠሩ ሠራተኞች መካከል ከፍተኛ የሆነ የክፍያ እና የጥቅማ ጥቅሞች ልዩነት መኖራቸውን ይህም አሠራር ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ የማግኘት መርሕን እንደሚጻረር በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ሠራተኞች በተገደበ የሥራ ሰዓት የመሥራት መብት ያላቸው ቢሆንም የኤጀንሲ ሠራተኞች በተለይም ሴቶችን ጨምሮ የጥበቃ አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ ከተደነገገው በቀን 8 ሰዓት እና በሳምንት 48 ሰዓት ያልበለጠ የመሥራት ግዴታ በላይ ያለትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲሠሩ እንደሚገደዱ ሪፖርቱ አመላክቷል።

ሠራተኞችን ከጉልበት ብዝበዛ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ዕረፍት እና ፈቃድ የማግኘት መብት በሕግ የተረጋገጡ ቢሆንም በጥበቃ ሥራ የተሰማሩት ሠራተኞች የሳምንት የዕረፍት ቀን የላቸውም።

ዕረፍቱን ሊተካ የሚችል የማካካሻ ክፍያ እንደማይከፈላቸው፣ ያለ በቂ ክፍያ በሕዝብ በዓላት እንዲሠሩ እንደሚደረጉ፣ በአንዳንድ ኤጀንሲዎች ሠራተኞቹ የዓመት እረፍት ፈቃዳቸውን ለመውሰድ በቅድሚያ ተተኪ ሠራተኛ እንዲያመጡ እንደሚደርጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የሕመም ፈቃድ እና የልዩ ፈቃድ እንደማይሰጥ እና የሚወስዱት ፈቃድ ከዓመት ፈቃዳቸው ላይ ተቀናሽ የሚደረግባቸው መሆኑ በሪፖርቱ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው።

እንዲሁም በሃዋሳ ከተማ በተደረገው ክትትል ሠራተኞች የወሊድ ፈቃድን ከሙሉ ክፍያ ጋር እንደማያገኙ እና ከወሊድ ሲመለሱም በፊት ይዘውት የነበረውን የሥራ መደብ እና ጥቅማ ጥቅም መልሰው ማግኘት እንደማይችሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የመደራጀት መብት ሠራተኞች መብቶቻቸውን በኅብረት ለማስጠበቅ እና የተሻለ የሥራ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል መብት ቢሆንም የኤጀንሲ ሠራተኞች ማኅበራት በተሟላ ሁኔታ አለመቋቋሙ እና ሠራተኞቹ ትርጉም ያለው ቅሬታ የማሰሚያ እና ውጤታማ ፍትሕ የማግኛ ሥርዓት ተጠቃሚ አለመሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር እና ሕጋዊ ያልሆኑ ኤጀንሲዎች መስፋፋት፣ ተጠቃሚ ድርጅቶች ዋና ትኩረታቸው ዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርብ ኤጀንሲ ማግኘት ላይ መሆኑ እንዲሁም ኤጀንሲዎችም ዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርቡ መሆኑ ለችግሮቹ እንደ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.