የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀውና “ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን” በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በጉባኤው ከመድረክ መወያያ ርዕስ ያቀረቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን በወደብ ጉዳይ የአካባቢው ሀገራት በአግባቡ እንዲያውቁ ቢደረግ ይህን መሰል ተቃውሞ ሊመጣ ይችል ነበር ወይ የሚል ጥያቄ ከአምባሳደሮች ተነስቶላቸዋል።
ለዚህም ምላሽ ሲሰጡ
በወደብ ጥያቄ ጉዳይ ላይ አልተገመትንም ፤ የተለያዩ ሀገራት ስለወደብ ስንናገር ጦርነት ውስጥ ይገባሉ ብሎ ሲገምቱን እኛ ግን በሰላማዊ መንገድ ነው የወደብን ጥያቄውን ለማድስፈጸም የተገኘነው ብለዋል።
ከሶማሌ ላንድ ጋር ስለነበረን ሁኔታ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በበቂ ሁኔታ አስረድተናል። ዩጋንዳና ኬንያን ጨምሮ የተለያዩ የኢጋድ አባል ሀገራት ጋር መረጃውን ይዘን ቀርበናል። ታንዛኒያና ጂቡቲ ስለጉዳዩ በአግባቡ እንዲያውቁ ተደርጓል፤ ጉዳዩን የኢጋድ አጀንዳ እናደርገዋለን ብለን ስናናግራቸው ነበር ሲሉ ሂደቱን ተናግረዋል።
በተለይ ጂቡቲ ስለወደብ ድርድሩ ሂደት ጭምር በአግባቡ ታውቅ ነበር ያሉት አማካሪው፤ ለአሜሪካኖች፣ ለሳውዲ አራቢያ፣ ለእንግሊዞች፣ ለዩናይትድ አረብ ኤምሬቶችም በተመሳሳይ አሳውቀን ሂደቱን ያውቃሉ። የማያውቁት ግን የሶማሊ ላንድ ሀገርነት ዕውቅና እና የአየር መንገድ ላይ ያላቸውን ሼር በተመለከተ ነው ሲሉ ድርድሩ በጥብቅ ሁኔታ ስለመከናወኑ ጠቁመዋል።
ለሚመለከተው መንግስት ስለሁኔታው ካስረዳን በኋላ የእራሳችንን ድርድር በማድረግ ነው የወደብ ጉዳዩን እያስፈጸምን ያለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት ጥያቄን አጀንዳ ማድረግ በመቻል በሰላማዊ መንገድ ለመሄድ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ተናግረዋል።