ኢትዮጵያ ትችት ሲያቀርቡባት የነበሩትን አፍ በማስያዝ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔትአስተዳደር ጉባዔን በስኬት አስተናግጃለሁ አለች።
ኢትዮጵያ እንደ ወትሮው የዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን በስኬት የማስተናገድ ልምዷን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ በአዲስ አበባ ዛሬ መካሔድ ጀምሯል፡፡
ይህ ጉባዔ በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ ከፍተኛ ዘመቻዎች ቢካሄዱም በጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራና በበሳል አመራር የኢትዮጵያን የአዘጋጅነት ሚና ለማስጠበቅና ጉባዔውንም በስኬት ለማስጀመር ተችሏል ነው ያለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
ኢትዮጵያ ከጊዜያዊ ችግሮች በላይ የሆነች ባለብዙ ተስፋ ሀገር መሆኗን የዓለምአቀፍ ጉባዔው ታዳሚዎች በተጨባጭ የሚመለከቱበትና የሚመሰክሩበት አጋጣሚንም ይፈጥራል ተብሏል።
የበርካታ ሀገራት ተወካዮች የሚሳተፉበት ይህ ጉባዔ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባትና ለዲፕሎማሲው መስክ ልዩ ትርጉም አለው ሲል ኮሙኒኬሽኑ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስሟን ለማጠልሸት ሲጥሩ የነበሩትን አካላት አሳፍራና የተደቀነባትን ፈተና ቀልብሳ ይህንን ዓለምአቀፍ ጉባዔ ማስተናገዷ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ ማንነት ያላት ሀገር ለመሆኗ ማሳያ መሆኑን ነው ተቋሙ ያስታወቀው።
የተለያዩ ሀገራት ጠቃሚ ልምዶች የሚቀርቡበት በመሆኑም በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ለተሰማሩ አካላትና ስራ ፈጣሪዎች ምቹ የልምድ ልውውጥና የትስስር መድረክ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በመሆኑም በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባዔ የሚታደሙትን እንግዶች በተለመደው ኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህል በማስተናገድ ሁሉም ዜጋ የሀገርአምባሳደርነቱን ማስመስከር ይጠበቅበታል ነው የተባለው።
ጉባዔው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ለማገዝ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለስኬቱ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መንግስት ጥሪውን አቅርቧል።