በሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ውጥረቶች የተከበበችው ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከ152 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ እንደምታስገባ አስታውቃለች።
ውጥኑን ይፋ ያደረገው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ነው።
የነዳጅ ፍጆታዋን ለመቀነስ በሚል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገቡ የወሰነችው ኢትዮጵያ እስካሁን ከ7 ሺህ የማይበልጡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብቻ አሏት።
በአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ የሚመራው የሃዩንዳይ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ዋነኛው የኤሌክትሪክተሽከርካሪ አምራች ድርጅት ሲሆን፤ እነደሃዩንዳይ አቅም ባይኖራቸውም ሌሎችም መገጣጠሚያዎች እየሰሩ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የሜትር ታክሲ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ በነዳጅ ከሚሰሩ ሌሎች የሜትር ታክሲ አገልግሎቶች በ60 በመቶ ያነሰ ዋጋን እያስከፈሉ ይገኛል።
በተለይ መነሻቸው 40 ብር የሆኑ የኤሌክትሪክ ሜትር ታክሲዎች አሁን ላይ የተጠቃሚዎቻቸው ቁጥር እያደገ ይገኛል።
ይሁንና በርካታ የአሽከርካሪ ባለቤቶች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከሁለትና ሶስት ዓመታት በኋላ ባትሪያቸው ይደክማል ለዚህም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃሉ በሚል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ምርጫቸው እንደማያደርጉ ሲገልጹ ይደመጣል።
ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት መለዋወጫቸውና ሞተራቸው ገብቶ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ላይ የ5 በመቶ የጉምሩክ ታክስ የምታስከፍል ሲሆን ሌሎች የታክስ ክፍያዎች ላይ የታክስ ክፍያዎችን ነፃ አድርጋለች።
በአንጻሩ ከውጭ አገራት ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ይጣልባቸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከምታስገባቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 4ሺህ 800ዎቹ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቡሶች እንዲሆኑ ማቀዱን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።