ኢትዮጵያ የታጥቁ ኃይሎች ወደማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚረዳ ኮሚሽን እንዲቋቋም ወሰነች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል። ከውሳኔዎቹ መካከል ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ይቋቋም የሚለው አንዱ ሆኗል።  

በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄዱ የቆዩት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ በወቅቱ ውይይት እንደተደረገበት ምክር ቤቱ አስታውቋል።

በተለይ በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል።

የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ በኢትዮጵያ የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ ለማስቻል ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ደንብ መዘጋቱ ተገልጿል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምክር ቤትም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑን አሳውቋል።

የሚኒስትርች ምክር ቤቱ በተጨማሪነት በመከላከያ ሠራዊት ረቂቅ አዋጅ ላይ መወያየቱ ተገልጿል።

መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የአገርን ሉአላዊነትና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጣ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ውስጥ እንደሚገኝና ውጤታማ መሆኑን ምክር ቤቱ ያወጣው መግለጫ አመላክቷል።

የመከላከያን  ሪፎርም የበለጠ ለማጎልበትና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ከሠራዊቱ ወቅታዊና የወደፊት ግዳጆች ጋር የሚጣጣም የህግ ማዕቀፍ ስላስፈለገ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ የሚተካ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተጠቁሟል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት  በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

ምክር ቤቱም የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሆኑ ታውቋል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.