የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓመቱን አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ) በተገኙበት አካሂዷል።
በወቅቱ መነጋገሪያ ጉዳዮች ከሆኑት መካከል ደግሞ የቀይ ባህር ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በወደብ ጉዳይ ላይ ያነሳችው ጥያቄ በሕግና በቢዝነስ ማዕቀፍ እንወያይ በሚል የተነሳ ጉዳይ መሆኑን ለሕዝብ እነደራሴዎች አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ወደብን በሚመለከት የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት የመጉዳትና በወረራ ፈላጎቷን የማሳካት አላማ እንደሌላት አስረድተዋል።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ ኤርትራና ሶማሊያ እንዲሁም ጂቡቲ እንደማይቀበሉትና የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ በጥ)ርጣሬ እነደሚመለከቱት በተለያየ መንገድ ሲገልጹት ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደግሞ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጉዳይ ከህግ ውጪ የሆነ ያልተገባ ጥያቄ አልጠየቀችም ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገራት አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም ሲሉ ጎረቤት ሀገራት ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።
እኛ ግጭት አላልንም ግጭት እንዳይመጣ እንነጋገር ነው ያልነው ሲሉም ተደምጠዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይ የተነሳው የኤርትራን ሉዓላዊነት ለመንካት አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዓባይን የምንገነባው የሱዳንን ሉዓላዊነት ለመንካት አይደለም በተመሳሳይ የቀይ ባህር ጥያቄም ለልማት እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይደለም ሲሉ በንጽጽር አስረድተዋል።
ወደብን በሚመለከት ተነጋግረን ህጋዊ መፍትሄ እናብጅ፤ ጥያቄውን ማንሳታችን እንደነውር ሊቆጠር አይገባም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥር እያደገ በመሆኑ ጉዳዩ ጊዜ ሳይሰጠው አሁኑኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ብለን እናምናለን በማለት ሃሳባቸውን ግልጽ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ከምስራቁም ከምዕራቡም ተስማምታ ማደግ የምታስቀድም ሀገር ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሁሉም ጋር በመተባበር ማደግን እንደግፋለን ሲሉ ተደምጠዋል።