እስከ 1ሺ ዶላር መላክ የሚያስችለው ነፃ የሃዋላ መንገድ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ አገራት የሚገኙ ሰዎች እስከ 1ሺህ ዶላር መላክ የሚችልበትን የሃዋላ መንገድ አስተዋወቀ።

ከሃዋላ አገልግሎት ክፍያ ነጻ ነው በተባለው አሰራር በሞባይል መተግበሪያና በቀጣይ ደግሞ በዌብሳይት መጠቀም እንደሚቻል የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ዛሬ በተደረገው መርሃግብር ገልጸዋል።

አዲሱን መተግበሪያ መጠቀም ተጨማሪ ወጪ ሳያስፈልግ በጊዜያዊነት ከካናዳ፣ እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ጣልያን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስዊድን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ እንግሊዝ እና ሳዑዲ አረቢያ  የሚገኙ ዜጎች የውጭ አገር ገንዘብ በቀላሉ መላክ የሚያስችል ነው።

ኢትዮጵያ በጥቁር ገበያ ዶላርና የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘቦች ከሚሸጡባቸው አገራት መካከል አንዷ ነች። ይህንን ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ለመግታት ባንኩ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማዘጋጀት የሃዋላ ስራውን ሲያከናውን ቆይቷል።

አሁን ላይ ደግሞ ‘ኢትዮ ዳይሬክት‘ (EthioDirect) የተባለ የሐዋላ አገልግሎት መስጫ ዘመናዊ ዲጂታል መተግበሪያ በማስተዋወቅ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አሳውቋል።

መተግበሪያውን ከጎግል ፕሌይ ስቶር በማውረድ መጠቀም የሚቻል ሲሆን በቀጣይ ደግሞ፤ በድረገጽ አማካኝነት አገልግሎቱን እንደሚያቀርብ ባንኩ ይፋ አድርጓል።

በቀጣይም ባንኩ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር በመነጋገር ወደ ሌሎች የዓለም አገራት አገልግሎቱን ለማስፋት ማሰቡን ጠቁመዋል።

በቀጣይ በርካታ አገራትን በማካተት መተግበሪያውን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ አቤ አሳውቀው፤ በውጨ አገራት የሚገኙ ዜጎች ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በሚልኩበት ወቅት ዲጂታል አማራጩን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በመተግበሪያው ከአምስት እስከ አንድ ሺህ ዶላር የሃዋላ ገንዘብ መላክ የሚቻል መሆኑን ጠቁመው የተላከውን ገንዘብ መቀበል የሚቻለው ለጊዜው ወደ ተቀባዩ የባንክ አካውንት ሂሳብ በማስገባት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ በሲቢኢ ብር ዋሌት እና በጥሬ ገንዘብ ደንበኞች ከባንኩ ቅርንጫፎች የሚወስዱበት አማራጭ ተግባራዊ እንደሚደረግ ባንኩ አስታውቋል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.