እንቦጭን ከጣና ሃይቅ የማስወገድ ስራ ተከናወነ

የጣና ሐይቅን የወረረዉ እንቦጭ አረም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና አረሙን ለማስወገድ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል።

በመንግስት እና በሌሎች አካላት የሚቀርቡ የተሳሳቱ ሪፖርቶች ህዝቡን “እንቦጭ አረም እየጠፋ ነዉ” ወደሚል መዘናጋት ዉስጥ እንዳስገቡት ያለፉት ሁለት ዓመታት አስረጂ ናቸው።

አሁን ላይ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር በስሩ ከሚገኙት 6ት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 2ሺህ በላይ ወጣቶችና እናቶች የተሳተፉበት ከጣና ሀይቅ የእምቦጭ አረምን የማስወገድ ስራ ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩ የከተማው አስተዳደር የመጓጓዣ ትራስፖርት በማዘጋጀትና በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በጎ ተግባር ፈጽመዋል፡፡

የጣና ሃይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ ኃላፊ ዶ/ር አያሌው ወንዴ ፤ ቀጣይነት ባለው መልኩ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ላይ ቁልፍ ሚና ያለው የጣና ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅ በርካታ ጥረቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

ጣና ሐይቅ ለሀገራችን የቱሪስት መናኸሪያ የገቢ ምንጭ በተለይ ደግሞ ለባሕር ዳር ከተማ ሁለንተናዊ የልማት አቅም የከተማዋ ሳንባ ነው።

ስለሆነም ሐይቁን መጠበቅና መንከባከብ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ሲሆን ጣናን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ አደራ መሆኑን የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።

ይሁንና እስካሁን አረሙን በህብረተሰቡ ጉልበት፣ በመዋጮ በተገዙ ማሽኖች እና በሌሎች የምርምር ዉጤቶች ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የተጠበቀዉን ዉጤት ማግኘት እነዳልተቻለ ዶክተር አያሌው ቀደም ብለው ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

ይልቁንም አረሙ ከጎርጎራ-ጣና ቂርቆስ ድረስ ባሉ የሀይቁ ዳርቻዎች ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ ይህም በብዝሃ ህይወት፣ በአሳ ማስገር፣ በእንስሳት መኖ፣ በቱሪዝም እና በእርሻ ስራ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉን ነው ያስረዱት፡፡ የህብረተሰቡን ጊዜ እና ጉልበት በማባከን በምርታማነት ላይ ችግር እያስከተለ ይገኛል፡፡

ለችግሩ እስካሁን የጎለበተ ትኩረት ሳይሰጭ በመቆየቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቀርጾለት የማስወገድ ስራዉ በአግባቡ አልተከናወነም ሲሉ ዶ/ር አያሌው  ገልጸዋል፡፡

የቆዩ የዕጽዋት ዝርያዎችን አረሙ በተወገደባቸዉ ስፍራዎች መትከል፣ ከልክ ያለፈ ግጦሽን ማስቀረት፣ አረም የማስወገድ ዘመቻውን በተከታታይነት በበጋ እና በክረምት ማከናወን እና ወደ ሀይቁ የሚለቀቁ ኬሚካሎችን መቀነስ እምቦጭን ለመቀነስ ዋና ዋናዎቹ መፍትሄዎች ሆነው ተቀምጠዋል።

ሶሳይቲ ፎር ኢኮ ቱሪዝም እና ባዮ ዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን ማህበር ተፈጥሮ በቆየዉ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና በድርብርብ ቢሮክራሲዎች ምክንያት የተፈለገዉን ያህል መስራት አልቻለም፡፡

ይህም ሆኖ ግን እንቦጭን ለማጥፋት ማሽን በመግዛት የራሱን ድርሻ ማበርከቱንም አልቀረም፡፡

ባለፉት አመታት ሐይቁ ከተደቀነበት አደጋ ለመከላከል በሰው ሀይልና በማሽነሪ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አረሙን መቀነስ የተቻለ ቢሆንም እንቦጭ ካለው ተፈጥሮአዊ የመስፋፋት አቅም የተነሳ ባልታየባቸው አካባቢዎች ጭምር በአዲስ መልክ መስፋፋት መጀመሩን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ስለሆነም ይኸንን የዘመናችን ጠላት የሆነውን እንቦጭ አረም ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለመላው የከተማዋ ነዋሪዎች በየጊዜው የዘመቻ ጥሪ እያስተላለፈ ይገኛል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.