እጅ ያልሰጠው ሰዓሊ

አርቲስት ወርቁ ማሞ በ1927 ዓ.ም በቡልጋ አካባቢ ነው የተወለደው፡፡ ገና ትንሽ ልጅ ሳለ አባቱ ወደ ጦርነት ዘመቻ በመሄዱ ከእናቱ ጋር ወደአዲስ አበባ መጥተው መኖር ጀመሩ፡፡

ወርቁ የ12 ዓመት ሲሞላው ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች በአንዱ በቸርችል አካባቢ ወዲህና ወዲያ ሲል ድንገት አንዲት የቆመች መኪና ከዓይኑ ውስጥ ትገባለች፡፡ ትንሹ ልጅም ጠጋ ብሎ መኪናዋን ይመለከታል፡፡ ከተከፈተው የመኪናዋ መስኮት ውስጥም አንድ የተጠቀለለ ወረቀት አይቶ ብድግ ያደርገዋል፡፡

አካባቢውን ባመሰው የፍንዳታው ድምፅ ሲሮጥ የመጣው ሰውም ትንሹን ልጅ አፈፍ አድርጎ ከሆስፒታል አደረሰው፡፡ ሁለቱ እጆቹ ክፉኛ ተጎድተው ስለነበረ ሕይወቱን ለማትረፍ የግዴታ መቆረጥ እንዳለባቸው ሐኪሞቹ ተናሩ፡፡ እጆቹም ተቆረጡ፡፡  ሰዓሊ የመሆን ትልቅ ሕልም የነበረው እንቦቃቅላው ወርቁ የሚያሳሱ እጆቹ በቦንብ የእሳት ነበልባል ሳቢያ ድባቅ ተመቱ። ቤተሰቦቹም ጭምር በእርሱ ተስፋ ቆረጡ።

የተጠቀለለውን ወረቀት ሲገልጠውም በውስጡ አንድ የማያውቀው ድቡልቡል ነገር አገኘ፡፡ ይህ ነገር ምን ይሆን በማለት ለማወቅ ጓጓና በእጁ እንቢ ቢለው ጊዜ በድንጋይ መቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ ለመፍታት ሲታገለው ግን በእጁ የያዘው ቦምብ ፈንድቶ ሀገር ምድሩን አናወጠው፡፡

ፈተናው መራራ የሕይወት ጽዋ ነበር። ይህ ልጅ  ሰዓሊ ለመሆን ይችላል ብሎ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እንኳን ተስፋ ያደረገ አነበረም። እርሱ ግን ባለልዩ ተሰጥኦ ሰዓሊ ሆነ፡፡

የማይቻለውን ችሎ ተፈጥሮንም  አሸነፋት፡፡ ገና በ12 ዓመቱ ለመሸከም የማይቻለውን የተሸከመው ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ዛሬ ላይ ትንግርተኛው የስዕል ሊቅ ለመባል በቅቷል፡፡ የኑሮ ችንካር ቢያደቀውም በዕድሜም 90ዎቹን ለመያዝ ተቃርቧል፡፡

በእጆቹ ሳቢያ የሐኪም ቤት ደጅ መርገጥ የዘወትር ሥራው ነበር፡፡ ቤት ገብቶ ለማድረግ የሚፈልገው የመጀመሪያውን ነገር ግን እርሳስ ለመጨበጥ መታገልና ከስዕል ፍቅር ጋር መፋጠጥ ነበር፡፡ እስራሱን አንስቶ ለመሳል በሞከረ ቁጥር ሁሉ ከተቆረጡት እጆቹ መካከል እርሳሱ ወደ መሬት ይወድቅበታል፡፡ ከአጠገቡ የማይጠፉት እናቱ ደግሞ ከመሬት እያነሱ ያስጨብጡታል፡፡ ከልምዳቸው አንጻር ሀሳብ እየሰጡ እንዲህና እንዲያ ብታደርገው ይሉታል፡፡ ያበረቱታል።

አንድ ቀን፤ ወደ አንድ ሰው በማምራት “ሰው ሠራሽና ባዕድ እጄን ይዤ ከምቸገር ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቡኝ” ያለባት ቀን ትምህርት ቤት የመግባት ዕድሉን አስገኘችለትና የሕይወቱን አቅጣጫ ቀየረችው፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱ ካቀና በኋላ ሰዓሊ የመሆን ሕልሙን ለማሳካት ምቹ ሆነለት፡፡

ወርቁ ልጅ ሳለ ጀምሮ የሥነ ስዕል ጥበብን አፍቅሮ እንዲኖር ያደረጉትም ወላጅ እናቱ ስለመሆናቸው ሁሌም ይናገራል።

ወርቁ ሌላም ፈተና ገጥሞት አልፏል። ጊዜው 1970 ዓ.ም ወቅቱ ደግሞ የክረምት ነበር። ከሚኖርባት ቤት ውስጥ በርካታ የቤተሰቡ አባላት ነበሩበት። አንድ ቀን ግን ከባዱን የሕይወት ውርጅብኝ ያዘለው የዝናብ ዶፍ ወረደ። የቤቱን ጣራ ግርግዳ በጎርፍ አጥለቀለቀው። ከቤተሰቡ መሐል የሁለት ሕጻናቶችን ነብስ ቀጠፈ።

በእርዳታ ጭምር ከውጭ ሀገራት የሰበሰባቸውን ልዩ ልዩ ቀለማትና የሚሠራባቸውን ቁሳቁሶች እያግበሰበሰ አጥረገረገበት። ብዙ ተስፋ ብዙ ሕልሙን አርግፎ ባዶውን ጨለማ አወረሰው።  የሕይወት ክምሩ ተንዶ ከላዩ ላይ ተከመረ። ግን የማያልፉት የለም አለፈ።ወርቁ በዕድሜ 60ዎቹን እስኪይዝ ድረስ ሁሉ በሕይወት ነበሩና በእያንዳንዱ ሥራዎቹ ውስጥ አሻራቸው አለበት። “ያለ እናቴ የትም ለመድረስ አልችልም ነበር” ይላል ወርቁ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከምንጊዜም ምርጥ ሁለት ሥራዎቹ መካከል አንደኛው “እናቶች” የተሰኘው ስዕሉ ቀዳሚው ነው፡፡ ሌላና ሁለተኛው ደግሞ “ተፈጥሮ” የሚለው ውብና ደማቅ የስዕል አበርክቶው ነው። ከእነዚህ በተለየ መንገድ አንድ ኢትዮጵያዊ ተመልክቶ በስሜት ንዝረት ሊገልጸው የሚችለው ሌላኛው ታላቅ ስዕሉ “ዓድዋ” ሲሆን ከሌሎቹ በተለየም በግዙፍ ሸራ ስሎ ለሀገሩ አበርክቶታል፡፡

በኢትዮጵያ የሥነ ስዕል ጥበብ ማኅደር ውስጥ አርቲስት ወርቁ ማሞ በሁለት ታላላቅ መስመሮች ላይ አርፏል። በሰዓሊነቱ ያበረከታቸው የስዕል ሀብቶቹ ከዘመን ዘመን ተሻግረው በየትውልዱ የሚተርፉ ናቸው። ጎን ለጎን ደግሞ ሠዓሊዎችንም የሚቀርጽ ታላቅ መምህር ነው።

ከቤተሰቦቹ አንስቶ እርሱን የተጠጉ ሁሉ የሥነ ስዕል ጠበበት ሆነዋል። ከግማሽ በላይ የሆነውን ዕድሜውን ያሳለፈው በመምህርነት ነው። አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ረዥሙን የሥራ ዘመን ያሳለፈበት ስፍራ ነው፡፡ ዕድሜው ገፍቶ በጡረታ እስከተገለለባት ዕለት ከዚያው ነበር፡፡ በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ያለውን ጥበብ ሁሉ ለተማሪዎቹ ሲያድል ቆይቷል። በጡረታ ከትምህርት ቤቱ ከወጣ በኋላም አሁንስ በቃኝ ብሎ እጁን አልሰጠም፡፡ በቀጥታ ወደ አቢሲኒያ የሥነ ጥበብና የሙያ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አቀና፡፡ ሁለቱ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በሥነ ጥበብ መምህርነት ከበርካቶች ደጅ ላይ ደርሷል። በገባባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ ከእግሩ ስር ቁጭ ብለው ጥበብን በመቅሰም የራሱን ደቀመዝሙሮች የሚያፈራ ጉምቱ አስተማሪ ነበር።

በሙሉ አካል ሆኖ ለመሥራት የሚያታክተውን ነገር እርሱ ግን በሁለት የተቆረጡ እጆቹ መሐከል ብሩሹን አሳርፎ ሌት ከንጋት በዚሁ ትግል ውስጥ ነው።ከ60 ዓመታት በላይ በስዕል ሥራ ውስጥ ሲቆይ የራሱ የሆነ ስቱዲዮ እንኳን አልነበረውም፡፡ በዚህም ከውሃና አቧራው ጋር ሳይቀር ሲንከራተቱ ከጥቅም ውጭ የሆኑ የስዕል ሥራዎቹ ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡

አርቲስት ወርቁ ማሞ ዛሬ በዕድሜ 90 ሊደፍን ተቃርቧል። ከእነዚህ መሐከልም ከሰባ በላይ የሆኑትን ያሳለፈው በስዕልና በመምህርነቱ ነው። ሲወድቅ ሲነሳ የሠራቸው የስዕል ሥራዎቹ ቁጥር ስፍር የላቸውም። እሱም ጥበብን ከእናቱ ተቀበለ፤ መልሶም ለልጆቹ ሁሉ አውርሷል። አካል እንጂ ስሜትና መንፈስ አያረጅም ካሉ ማሳያው ወርቁ ማሞ ነው፡፡  

netevm.com