በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ጊዜው የቅዝቃዜ ወቅት ነው። በተለይ በአሜሪካና በካናዳ የወቅቱ በረዶ በማየሉ ቅዝቃዜው ከፍተኛ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።
ወቅቱ ደግሞ በኢትዮጵያ የገናና የጥምቀት በላዓት የሚከበሩበት በመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች ለአስደሳች ጉብኝት ብሎም ቅዝቃዜውን ለማምለጥ ወደኢትዮጵያ እንደሚመጡ ይጠበቃል።
በታህሳስ ወር መጨረሻ የሚከናወነው የገና በዓል በተለይ በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ አብያተክርስቲያናት በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። የጥምቀት በዓል ደግሞ የአብያተክርስቲያናት መናገሻ በሆነችው ጎንደር በተዋበ ሁኔታ እነደሚከበር ይታወቃል።
ታዲያ ዳያስፖራዎችና የአገር ውስጥ ነዋሪዎች ሁለቱን በዓላት ሲያከብሩ ከዋነኛው የቱሪዝም መዳረሻዎች ባለፈ በተጓዳኝ ምን አይነት አማራጮችን ማማተር ይችላሉ ለሚለው የአስጎብኚ ድርጅቶችና የቱሪዝም ባለሙያዎች መልስ አላቸው።
ላላሊበላ ለገና በዓል ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅታለች። በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ቱሪስቶች የሚያርፉባቸው 45 ሆቴሎችን እና ተጨማሪ ማደሪያዎች ላይ ዝግጅት ተደርጓል።
ከዋክብተ- ሮሃ በታህሣሥ 29 የገና በአል በቤተ-ማርያም ማሚ ጋራ ላይ እንደ ከዋቅብት ፍክት ድምቅ ብለው የድንግል ማርያምን ልጅና ቅዱስ ላሊበላን ሲያመሠግኑ ወረብና የተለያዩ ዝማሬዎችን ሲያቀርቡ ማየት ያስደስታል።
ላላሊበላ ለገና በዓል ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅታለች። ጎብኚዎቿ ታዲያ ከላሊበላ በተጨማሪ ጣሪያው ክፍት ሆኖ ዝናብ የማያስገባበትን ታሪካዊውን ደብረ አሮን ታሪካዊ ገዳምንና የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ለ7ቀን ያረፈባት የአሸተን ማርያምን በቅርብ ርቀት ተጉዘው መጎብኘት ይችላሉ።
ከላሊበላ 80 አመት ቀድሞ በዕምነበረድና እንጨት የታነጸ ፣ ከላሊበላ 42 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ውስጡ ባማሩ ስዕሎችና የከበሩ ድንጋዮች የተሽቆጠቆጠ በዋሻ ውስጥ በባህር ላይ የተሰራውን ይምርሀነ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን መጎብኘት አስደሳች ነው።
ለልደት በዓል ላሊበላ ሲመጡ እጅግ በተለየ ባህላዊ የግንባታ ጥበብ የተሰሩና የላስታን መልክዓ ምድር መቃኘት አስደሳች እንደሚሆን አያጠራጥርም።
በላሊበላ የሚገኙ ባህላዊ የዕደጥበብ ውጤቶችም ለበዓሉ ልዩ ትውስታን የሚያድሉ ናቸውና የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ።
ከላሊበላ የገና በዓል ባለፈ ጥምቀት በጎንደር በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
ዓለም አቀፉ የትምህርት፣የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በተለይም ደግሞ በታላቁ ጎንደር በድምቀት የሚከበረውን የጥምቀት በዓልን በማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ አካቶታል።
ጎንደር ከተማን ሐይማኖታዊና ታሪካዊ ክዋኔዎች እንዲሁም ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጎብኘት በየዓመቱ በርካታ ቱሪስቶች ይጎርፋሉ።
በተለይ በጥምቀት በዓል ወቅት የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ዜጎች ጎንደርን ማየት ይናፍቃሉ።
የዘንድሮውን የጥምቀት በዓልና በጎንደር ከተማ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው 13ኛው የባህል ሳምንት ለማክበር እየተሰሩ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት ውይይት ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ሃላፊዎች እንዲሁም የላሊበላና የጎንደር ከተማ አስተዳደሮች ለበዓላቱ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ከጎንደር በፋሲል ግቢ የሚገኙ ግብረ ህንጻዎችን እና በደብረ ብርሃን ስላሴ እነዲሁም በከተማዋ ከሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች በተጨማሪ የደባርቅ ከተማንና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን መጎብኘት ይቻላል።
ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የጎንደር ዙሪያ ወረዳ እና አካባቢው የጎንደሪያን ስልጣኔ መነሻና ለ34 ዓመታት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ መናገሻ፣ የንግድና የፖለቲካ ማዕከል በመሆን አገልግሏል፡፡
በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከደንቀዝ /ጎመንጌ/፣ ባህሪ ግንብ፣ ጉዛራ ቤተ-መንግስትና ጎባጢት ድልድይ ባሻገር አምባ ማርያም ጥንታዊ ገዳም፣ ደምጎርሳ ጊዮርጊስ፣ አጼ ገላውዲዎስ ግራኝ አህመድን ድል ያደረጉበት ወይና ደጋ/ግራኝ በር/፣ ምንዝሮ ተክለ-ሀይማኖት፣ ደብሳን ግንብ፣ ሰንደባ ተክለ ሀይማኖት፣ አርባይቱ ከሰው ሰራሽ ቅርሶች መካከል ሲሆኑ ከተፈጥሯዊ የመስህብ ቦታዎች የጣና ሀይቅና ሌሎችን ቅርሶች በውስጡ አቅፎ ይዟል።
ሌላኛው ቅርስ የሚገኘው በደብረ ሲና ማርያም አንድነት ገዳም ነው። ገዳሟቅ 703ኛ ዓመት ክብረ በዓል አክብራለች።
በጣና ሐይቅ ሰሜን አቅጣጫ ከባህር ዳር ከተማ በጣና ሐይቅ 78 ኪሎ ሜትር ከጎንደር ከተማ በአዘዞ 64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጎርጎራ ከተማ ትገኛለች።
ከ703 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋዋ ደብረ ሲና በ1312ዓ.ም በአፄ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግስት ነበር የተመሰረተችው፤ ለጎብኚዎች ምቹ ስፍራ ነች።
ጥር ወር ልዩ የቱሪዝም ወር ነው” ያሉት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ ናቸው። ዕውነትም ከገና በዓል ቀጥሎ ጥምቀት በጎንደርና በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ፣ የግዮን በዓል በሰከላ፣ 83ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ፣ የመርቆሪዮስ በዓል በደብረ ታቦር በዚሁ ወር ከሚከበሩትና በርካታ ቱሪስቶች ከሚታደሙባቸው በዓላት መካከል ናቸው።