ከተራና ጥምቀት በኢትዮጵያ

ጥምቀት” ለሚለው ቃል መነከር፣ መታጠብ የሚሉ ትርጓሜዎች ይሰጣሉ፡፡ የጥምቀት ዋዜማ የሆነው ከተራ ደግሞ ውኃውን/ባህሩን አገደ፣ ከበበ፣ አጠራቀመ እንደማለት ነው።

በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር ጥር 11 ቀን፣ 31 ዓ.ም. (5531 ዓመተ ዓለም) በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ እንደሆነ ያነበብኳቸው መንፈሳዊ መጻሕፍት ያብራራሉ፡፡

በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ክርስትያን አማኞች ዘንድ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ ናቸው።

የኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ የብዙ ቱሪስቶችን ቀልብ እንደሳበ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው።

ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደየአመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።

የጥምቀት በዓል ልክ እንደ መስቀል በዓል ሁሉ ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በ UNESCO በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።

ከጥምቀት ዋዜማ ማለትም በየዓመቱ ጥር ፲(10) ቀን ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲኾን ምእመናን ውኃውን በመከተር (በመገደብ ) ስለሚውሉ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር ፲፩(11) ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ነው፡፡ ይኽ ውኃ የሚከተርበት ሥፍራም “ባሕረ ጥምቀት” ወይንም “የታቦት ማደርያ” ተብሎ ይጠራል፡፡

በዚኽ የከተራ ዕለት ካህናቱ ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ላይ አክብረው ወደ ባሕረ ጥምቀት መሄዳቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መሄዱን ለማዘከር ነው፡፡

የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ባሕረ ጥምቀት ለመሄድ ሲወጣ “ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት፡፡” የሚለው የሚዘመረውም ይኽንን እውነት ለመግለጽ ነው፡፡

በተጨማሪም በጉዞ ላይ “እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ ኢየሱስ፣ መጽአ ቃል እምደመና ዘይብል” የሚሉትና ሌሎች መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም በጎንደር በባቱና በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከተራና ጥምቀት በዓላት በዓደባባይ በድምቀት ይከበራሉ። በርካታ ቱሪስቶችም ዕለቶቹን ምክንያት አድርገው ወደኢትዮጵያ ይመጣሉ።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.