ከኦንላይን አጭበርባሪዎች መጠንቀቅ ይገባል

ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ እየተዟዟሩ ስለሚገኙ የማጭበርበሪያ ሊንኮችን በተመለከተ ህብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድ ግላዊ መረጃዎችን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቅ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሳስቧል።

ሁሉም ሰው የኢንተርኔት ዓለም እውነታዎችን መረዳትና ማወቅ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

በኦንላይን የሚደረጉ ግብይቶች፣ የመረጃ ልውውጦችና የምናጋራቸው መረጃዎች እንዴት በእውነተኛ ህይወት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ማወቅና መገንዘብ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በኦንላይን ከምናጋራውም ሆነ ከምንከፍተው ሊንክ መጠበቅ የግላችንን ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

ከሰሞኑ በርካታ የቴሌግራምና ፌስቡክ አካውንቶች ላይ እውነት የሚመስሉ ነገር ግን ከጀርባቸው አንዳች ነገር የያዙ ሊንኮች ወይም መልዕክቶች ሲዘዋወሩ መመልከቱን አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

የእነዚህ ሊንክ ፈጣሪዎች ግላዊ መረጃ ለመውሰድ በማሳብ እጅግ አሳማኝና ትክክል የሚመስሉ መረጃዎችን በማጋራት ሊንኩ ሲከፈት ሙሉ ስም፣ የቤት አድራሻና ስልክ ቁጥር በመጠየቅ ስለግለሰቡ መረጃ ካገኙ በኃላ ለቀጣይ ጥቃት የሚዘጋጁበት መንገዶች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

በኦንላይን መረጃ ከመስጠታችን አስቀድሞ የተቀባዩን ማንነትና ትክክለኛነት ማረጋገጥ የግድ ያስፈልጋል ነው የተባለው፡፡

የሳይበር ወንጀለኞች የመረጃ ግላዊነትን ይጥሳሉ ያለው አስተዳደሩ ምክንያቱም ግላዊ መረጃ በጥቁር ገበያ ይሸጣል፣ብዙ ዋጋ ያወጣልም ነው ያለው። ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰረቀ መረጃ በጥቁር ገበያ በተለያዩ አገሮች እንዳሉም ገልጿል።

የሳይበር ወንጀለኞች በኦንላይን የሚሸጡት የመረጃ አይነቶች የሞባይል ስልክ ቁጥሮች፣ የኢሜይል አድራሻዎች ፣የክሬዲት/ATM ካርድ/ ባንክ አካውንት ቁጥሮች፣ የIP አድራሻዎች፣ PIN Code/የይለፍ ቃልና ሌላ የግል መረጃ ይገኝበታል።

በመስመር ላይ (online) መረጃ ከመስጠታችን አስቀድሞ የተቀባዩን ማንነትና ትክክለኛነት ማረጋገጥ፤ የተላኩትን ሊንኮች ከመክፈታችን በፊት የላከውን አካል ማንነት ማጣራት፣ የተላከው ሊንክ ከምናውቃቸው ሊንኮች ጋር አንድ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም ከተጠራጠርን ፈጽሞ ሊንኮቹን አለመክፈት መውሰድ ያለበት የጥንቃቄ እርምጃ መሆኑን አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

ህብረተሰቡ ከኦንላይን አጭበርባሪዎች ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሳስቧል።

netevm.com