ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት (ITU) የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤውን ከመስከረም 22 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚያካሂድ አሳውቋል።

ከኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚካሄደው ጉባኤ “ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለዘላቂና ፍትሐዊ መጻኢ ጊዜ የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ማፋጠን” የሚል መሪ ሀሳብ ይዟል።

ጉባኤው በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣትና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።  

የአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለአህጉሪቷ መጻኢና ዘላቂ የዲጂታል እድገት እንዲሁም ለዓለም አቀፍና አህጉራዊ የልማት ግቦች መሳካት ያለው ሚና ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት፣ በአፍሪካ እየተተገበሩ ያሉ የዲጂታል ትስስር ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ደረጃን የተመለከቱና ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ውይይት ይደረግባቸዋል ተብለው ከተያዙ አጀንዳዎች መካከል ናቸው።

በጉባኤው ላይ የሕብረቱ የአፍሪካ አባል አገራት ሚኒስትሮች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትና የልማት አጋሮች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።

ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት አንዱ ሲሆን የተቋቋመው እ.አ.አ በ1865 ነው።

ዋና መስሪያ ቤቱን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው ሕብረቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ 193 አባል አገራት ያሉት ሲሆን፤ በዋናነት በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረቱን በማድረግ ዓለምን የማስተሳሰር ግብ ይዞ በመስራት ላይ ይገኛል።

netevm.com