የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች ዝቋላ ገቡ

በታዋቂው የዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም በተለምዶ ዝቋላ አቦ በተባለው አካባቢ የፌዴራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎች መሰማራታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮጵያን ቪው ተናግረዋል።

የዝቋላ አቦና አካባቢው ከትላንትና ጀምሮ በታጠቁ ሃይሎች ከበባ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ነዋሪዎቹ አሳውቀዋል።

የታጠቁ ኃይሎቹ የሸኔ አባላት መሆናቸውን በመግለጽ፤ የጥንታዊውን ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም አገልጋዮችን ይዘው እንደነበር ነዋሪዎች አስረድተዋል።

እሁድ ከሰዓት በኋላና ምሽተሩን በአካባቢው በተሰማራው የፌዴራል ጸጥታ ሃይሎች ምክንያት በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም  መስፈኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከአዲስአበባ በቅርብ ርቀት የሚገኘውና በርካታ መናንያን የሚኖሩበት ገዳም በተራራማው አካባቢ በርካታ አርሶአደሮች ይኖራሉ።

ከአዲስ አበባ 80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ውብና በደን የተሸፈነው የዝቋላ ተራራ ከባህር ጠለል በላይ 2989 ሜትር ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው።

ተራራው አናት ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘንድ የሚከበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ለአንድ መቶ ዓመታት እንደጸለዩበት የሚታመን ሐይቅ ይገኛል።

ዝቋላ አቦ ገዳምና የዓመታዊ ንግድ በዓል አክባሪዎች

ይህንን ታሪካዊ ቦታ ለመሳለም በተለይ ጥቅምት 5 እና መጋቢት 5 ቀን በርካታ የኦረቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች በተራራማ ስፍራ ላይ ወደሚገኘው ጥንታዊ ገዳም ይሄዳሉ።

የገዳሙን ተራራማ ስፍራ ለመውጣት ጎብኚዎች የሁለት ሰዓት የእግር ጉዞ የሚሄዱ ሲሆን ከቅርበ ጊዜያት ወዲህ ተሽከርካሪ የሚያስገባ ጥርጊያ መንገድ ገዳሙ ደጃፍ ድረስ ተሰርቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የፌዴራል ሃይሎች አካባቢው ላይ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ወድቀው ቆይተዋል፣ አንዳንዶችም ንብረታቸውን ጥለው ወደገዳሙ መግባታቸውን በስልክ አሳውቀው ነበር።

አሁን ላይ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መድረስ የተነሳ የተረጋጋው አካባቢ በዘላቂነት ሰላሚ ሊጠበቅ እነደሚገባ ነዋሪዎቹ አሳስበዋል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.