የሚኒስትሮች ምክር ቤት እየተባባሰ የመጣውን የአማራ ክልል ፀጥታ በተመለከተ ተወያይቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ማወጁን ይፋ አድርጓል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ23ኛ መደበኛ ስብሰባው በክልሉ የታየው የጸጥታ ችግር ከአማራ ክልል አስተዳደር አቅም በላይ መሆኑን አንስቷል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በክልሉ ያለው ችግር ከአቅማችን በላይ ነው የፌዴራል መንግስት ይታከልበት ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ደብዳቤ መጻፋቸው የሚታወስ ነው።
የሚኒስትሮክ ምክር ቤትም የህዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በክልል አስቸኳይ ግዜ ያስፈልጋል በሚል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ከዚህ በመቀጠል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እነደሚጠራና አዋጁን እነደሚያጸድቀው ይጠበቃል።
በክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ያተተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰላም ማስፈን አስፈላጊ ነው በሚል ሃሳብ አስቸኳይ ጊዜውን ማወጁን አስታውቋል።
በአማራ ክልል ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋና በተለያዩ አካባቢዎች ከመከላከያ ሰራዊትና ከአድማ በተና ፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት በትርካታ መንገዶች መዘጋታቸውንና የሰው ሕይወት መጥፋቱ የሚታወቅ ነው።