የምክር ቤት አባላት አመኔታ ሲያጡ የሚነሱበት መመሪያ

ዜጎች በመረጡት የሕዝብ ተወካዮች አባል  ላይ አመኔታ የሚያጡ ከሆነ የይውረድልን ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉበት ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በመመሪያው ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ፖርቲዎች መመሪያውን መንግስት ያለአግባብ ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

ረቂቅ መመሪያው ግን በእራሱ በምክር ቤቱ ቀርቦ መጽደቅ ያለበት ሕግ ነው።

በ7 ምዕራፎችና በ41 አንቀጾች የተደራው ረቂቁ በቀጣይ የሚጸድቅ ከሆነ በፌዴራል እና በክልል ምክር ቤትአባላት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

አልበጀንም ይውረድልን የሚል ጥያቄ የሚቀርብበት አባል በተመረጠበት ዓመት እና በመጨረሻው ዓመት ጥያቄው ሊቀርብበት እነደማይችል በረቂቅ መመሪያው ላይ ሰፍሯል።

 ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ብቻ በመጀመሪያው ዓመት በተወካዩ ላይ የይውረድልን ጥያቄ ማቅረብ የሚቻል መሆኑም ተመላክቷል።

ጥያቄው ሊቀርብ የሚችለው አንድ የምክር ቤት አባል በተወዳዳረበት የምርጫ ክልል ሲሆን፤ ከ100 በላይ መራጮች ተፈራርመው ጥያቄውን ማቅረብ እንደሚችሉ ረቂቁ ላይ ተጽፏል።  

ጥያቄውን የሚያቀርቡ መራጮችም በዋናው ምርጫ ወቅት በምርጫ ጣቢያ የተመዘገቡና የመረጡ  መሆን ይኖርባቸዋል።

በግልጽም ምክንያታቸውን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ጥያቄያቸው በቦርዱ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ  በምርጫ ክልሉ የሚገኙ ከ15 ሺህ በላይ መራጮች ስለመስማማታቸው የሚያስፈርሙበት ወረቀት ይሰጣቸዋል፤ 15 ሺውም ከፈረሙበት በቃ ያ ተመራጭ የስልጣን ዘመኑ አበቃ ማለት ነው።

ከዚያም በምትኩ ሌላ ተመራጭ እነዲገባ ይደረጋል፤ ይህ ረቂቅ መመሪያ በቀጣይ ወደስራ የሚገባ ከሆነ ብዙ ሹም ሽሮችን ሊያሳይ እንደሚችል ይገመታል።   

netevm.com