የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ 600 ቶን ቆሻሻ እያቃጠለ ነው

የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ  ለጊዜው የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ቢያቋርጥም ሠበቀን በአማካይ 600 ቶን ቆሻሻ በማቃጠል ላይ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ብሩክ ኤባ እንዳስታወቁት ከአዲስ አበባ ከተማ የሚሰበሰበውን ደረቅ ቆሻሻ በዘመናዊ መንገድ በማቃጠል የአካባቢ ብክለትን በማያባብስ መልኩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል  

ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ እየተከናወነ ያለውን ጥገና ሥራ እስከ ታህሳስ መጨረሻ ባሉት ጊዜያት ውስጥ በማጠናቀቅ ጣቢያውን ኃይል ወደ ማምረት ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ጣቢያው ኃይል ወደ ማምረት ሲመለስ ቆሻሻ የመቀበል እና የማቃጠል አቅሙን በመጨመር ለአካባቢ ጥበቃና ለዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የቆሻሻ ማጣሪያ (leachate treatment plant)፣ የስቲም ተርባይንና ጀነሬተር ጥገና እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡

ወደ ኃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚመጣው የቆሻሻ ጥራት ከሚጠበቀው ደረጃ በታች መሆኑ፣ ማመንጫ ጣቢያው በባህሪዩ የተለየ በመሆኑና በየሲስተሞቹ የሠለጠነ ባለሙያ እጥረት በመኖሩ ብልሽት እንደሚያጋጥም ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የጥገና ሥራው የጣቢያው ባለሙያዎችን ጨምሮ ከኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን የሥራ ዘርፍ በተውጣጡ የተለያዩ ባለሙያዎች እየተከናወነ ነው፡፡

የጥገና ሥራው በራስ አቅም መከናወኑ ለውጭ ሥራ ተቋራጭ ለጥገና ሥራ የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ በተጨማሪ የባለሙያዎችን በራስ የመተማመን አቅም ለማሳደግ እና ወደ ፊት የሚያጋጥሙ ተመሳሳይ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የጥገና ሥራው በውጭ ሥራ ተቋራጭ ይከናወን ቢባል አንድ ተርባይን ከነጀኔረተሩ ከፍተሻ ጀምሮ ለመጠገን 75 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅም ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

ለጣቢያው የጥገና ሥራ የሚያገለግሉ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማቅረብ ተቋሙ “China National Electric Engineering Co.LTD” ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር የማዕቀፍ ግዥ የውል ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.