ትናንትና የጀመረው በሠሜን ሸዋ በተለይም ጀውሀ በተባለ አካባቢ በሚገኝ የፌዴራል ፖሊስና የአማራ ልዩ ሃይል ካምፕ ላይ በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት ከ30 በላይ የፀጥታ ሃይሎች ሕይወታቸውን እንዳጡ በአካባቢው የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በቡድን መሳሪያ የታገዘው ጥቃት በሸዋሮቢት፣ አጣዬ ፣ሰንበቴ ና በአካባቢው በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በተቀናጀ መልኩ መፈጸሙን የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ጥቃቱ አሁን ላይ ጋብ ያለ ቢመስልም አልፎአልፎ የጥይት ድምጾች እንደሚሰሙ ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።
በተለይ አጣዬ ከተማ በተደጋጋሚ ጊዜ ለተኩስ ጥቃት የተጋለጠች ከተማ ነች። ባለፉት ጊዜያት በነበሩ ጥቃቶች በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት የሚደርሱ ጥቃቶች ቤት ማቃጠልና የንጹሃን ግድያንም ያስከተለ ነበር።
አካባቢው ለረጅም ጊዜ በመከላከያ ኮማንዶዎች የሚጠበቅና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆኖ እንዲረጋጋ የተደረገ ስፍራ ነው። ጥቃቱን በተደጋጋሚ የሚፈጽሙት የሸኔ ሽብር ቡድን አባላትና በከብት ግጦሽ እንዲሁም በመሬት ምክንያት ግጭት ውስጥ የገቡ የአካባቢው ታጣቂዎች መሆናቸውን አንዳንድ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
አጣዬ ትናንት የነበረው የቤት የማቃጠልና ንፁሃንን የማሰቃየት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ የቆመ ሲሆን የክልሉና የፌደራሉ የፀጥታ ሀይሎች አካባቢው እያረጋጉ ነው።
በርካቶች ጥቃቱ ሲፈጸም ወደ መሀል ሜዳና ጣርማ በር የሄዱ ነዋሪዎች ነበሩ። በጥቃቱ ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴና ወልዲያ የሚወስደው ዋና መንገድ ዝግ ሆኗል።
ናሪዎች ወቅት እየጠቀቀ የሚያገረሸው ጥቃት በአካባቢው አመራሮችና ባለሃብቶች ድጋፍ ሊኖረው ስለሚችል በተለይ የኦሮሞ ብሄረሰብና የሰሜን ሸዋ አስተዳደር አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉዳዩ ላይ ጠንካራ የደህንነት ሥራ አላከናወነም በሚል በነዋሪዎች የተተቸው የአማራ ክልላዊ መንግሥት መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው በፀረ ሰላም ኃይሎች አማካይነት ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 9፡ 00 ሠዓት አካባቢ ጀምሮ በኤፍራታና ግድም ወረዳ ጀውሃ ቀበሌ በሚገኘው የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ እና በፌደራል ፖሊስ አባላቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል።
የፀረ ሰላም ኃይሎች በጸጥታ ኃይሎቻችን ላይ የከፈቱትን የአፈሙዝ ላንቃ ወደ ንጹሃን ዜጎች በማዞር በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ እያደረሱም ይገኛል።
በተለይም በኤፍራታ ግድም፣ አጣየ፣ ሰንበቴ፤ ጀውሃ እና በሸዋሮቢት ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ቀበሌዎች የፈጸሟቸውን ጥቃቶች የብሔር መልክ ያለው እንዲመስል በማድረግ በሕዝብ መካከል የብሔር ግጭት ለማስነሳት ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራዎችን እየፈጸሙ ይገኛል ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
መንግሥት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ በዚህ የፀረ ሰላም ቡድን እና ተባባሪዎቹ ላይ ሕጋዊ፣ የተጠና፣ በማያዳግም መልኩ የህግ የበላይነትን በማስከበር የክልሉን ሕዝብ ሠላም፣ ደህንነትና አንድነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣል ሲል ክልሉ አስታውቋል።