በኢትዮጵያ ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተዋጊዎች ጋር በተያያዘ ትጥቅ አውርደው ወደሰላማ ህይወት እንዲመለሱ በሚል የተቋቋመው ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽኑ ተመሳሳይ ስራዎችን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ ትጥቅ ባወረዱ ተፋላሚዎች ላይ እነደሚያከናውን አስታውቋል።
በቤኒሻንጉል የቀድሞ ተዋጊዎች የመልሶ ማቋቋም ያለመ የምክክር መድረክ ላይ አምባሳደር ተሾመ ቶጋና የክልሉ አመራሮች በተገኙበት በአሶሳ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ በአጠቃላይ የነበሩ ግጭቶችንና ችግሮችን ለመፍታት ውይይትን በማስቀደም ከቀድሞ ተዋጊዎች ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጓል። በኋላም ትጥቅ ለማውረድ በመስማማት በሰላማዊ መንገድ ወደሀገር ውስጥ ገብተዋል ብለዋል።
አሁን ላይ ደግሞ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ምን አይነት ሂደት ያስፈልጋል ምን አይነት ሁኔታዎች መስተካከል አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ከተሃድሶ ኮሚኝሽኑ ጋር በጋራ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎች ለማቋቋም የተጀመረ የተለያየ ስራ መኖሩንና ለዚህም ተግባር የቤኒሻንጉል ክልልና የፌዴራል መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በክልሉ ይንቃሳቀሱ የነበሩ የጉህዴን ታጣቂ አመራሮች ከቤኒሻንኩል ክልል አመራሮች ጋር የሰላም ስምምነት ፈጽመዋል። በኋላም ታጣቂዎቻቸው እጃቸውን ለመንግስት ወታደሮች እየሰጡ ወደሰላም መመለሳቸውን ሲገለጽ ቆይቷል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፤ የስራቸው ዋና አላማ የቀድሞ ተዋጊዎች ራሳቸውንና ሀገራቸውን ሊጠቅሙ በሚችሉበት ደረጃ እንዲቋቋም ማድረግና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይ ለሚከናወኑ የተሃድሶ ስረዎች የሚረዱ የዝግጅት ክንውኖች እነደሚያስፈልጉ ገልጸው፤ ለዚህም ከክል አመራሮች ጋር በጋራ ስራዎች እነደሚከናወኑ ይፋ አድርገዋል።
በውይይቱ የወቅት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይሳቅ አብዱልቃድር ተገኝተዋል።
በቤኒሻንጉል ካማሺ እና መተከል ዞኖች ሲንቀሳቀስ የነበረው የጉህዴን ታጣቂ ቡድን በደፈጣ በርካቶች ላይ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን የሚታወስ ነው። አሁን ላይ በርካታ የቡድኑ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደሰላማዊ እንቅስቃሴ በመመለሳቸው አካባቢው በአንፃራዊነት የተሻለ ሰላም ማግኘቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት እና በክልሉ ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የሠላምን ስምምነት በ2023 ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ተፈራርመዋል።