የናዝሬት ስኩልና  የባለስልጣኑ ውዝግብ

በአዲስ አበባ 70 ደረጃ አካባቢ የሚገኘውና ሴቶችን ብቻ በማስተማር የሚታወቀው ናዝሬት ስኩልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን  መካከል ውዝግብ ተፈጥሯል።

በውዝግቡ የተነሳ የናዝሬት ስኩል መደበኛ ተማሪዎች ትምህርት አልጀመሩም።  

ለችግሩ መንስኤ የሆነው ደግሞ ትምህርት ቤቱ በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል 15 ተማሪዎች ውጤት አጭበርብረዋል በሚል በዲሲፕሊን ማገዱ ነው።

በናዝሬት ትምህርት ቤት ልጆቻቸው የታገዱባቸው የተማሪ ወላጆች ደግሞ ጥያቄያቸውን ይዘው ለአራዳ ክፍለ ከተማ የትምህርት ጽህፈት ቤት ቅሬታ አቅርበዋል።

ቅሬታውን የሰማው የአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት፤ ልጆቻቸው የታገዱባቸውን ወላጆችና ናዝሬት ስኩልን ለማነጋገር ጥሪ አድርጎ የትምህርት ቤቱ የቦርድ አባላት አልቀረቡም።

ትምህርት ቤቱ በበኩሉ ጉዳዩን ቀርቤ ለማስረዳት ሞክሬ ነበር ነገር ግን የአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት የታገዱት ተማሪዎች በምን ምክንያት እንደታገዱ ሳይረዳ ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንድንመልሳቸው ጫና እያደረገብን ነው ሲል ለጽ/ቤቱ በፃፈው ደብዳቤ አቅርቧል።

 አለመግባባቱን ተከትሎ የአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ጉዳዮን የበላይ አካል ወደ ሆነው የአዲስ አበባ የትምህርትና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤት ወስዶታል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የታገዱ ተማሪዎች ወላጆችንና ትምህርት ቤቱን በጋራ ለማነጋገር ሞክሮ እንዳልተሳካ ገልጿል።

ይህንን ተከትሎ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የትምህርት ቤቱን ዕውቅና ፈቃድ አግዶ የነበረ ሲሆን በነሃሴ 19  ቀን 2015 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ትምህርት ቤቱ የታገዱ ተማሪዎችን ለመመለስ ተስማምቷል በማለት የዕውቅና ፈቃድ እገዳውን ማንሳቱን አሳውቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የዕውቅና ፈቃድ እገዳውን አንስቻለሁ በማለቱ ትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ምዝገባ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም እንደገና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምዝገባ አቁሙ የሚል የቃል ትእዛዝ መምጣቱን በመስከረም 4  ቀን 2016 ዓ.ም ለወላጆች በማሳወቅ ምዝገባ በይፋ ማቆሙን ገልጧል።

በዛሬው :ለት ወላጆች መደበኛው ትምህርት እንዲጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርበው መነጋገራቸው ተመላክቷል።

ወላጆች በበኩላቸው የታገዱት ተማሪዎች ተመልሰው እንዲመዘገቡና አዲስ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ተቋቁሞ ታግደው የነበሩት ተማሪዎች ጉዳይ በድጋሚ እንዲታይ እንደተወሰነ ለቲክቫህ ጠቁመዋል።

ናዝሬት ስኩል የተማሪዎቹ የዲሲፕሊን ጉድለት ምን እንደነበር ባይገልጽም ሰኞ መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ትምህርት እንደሚጀመር አሳውቋል።

netevm.com