የአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን እሑድ በአዲስ አበባ ይሸኛል

  • የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ  ይፈጸማል

አቶ ግርማ የሺጥላ

የአማራ ክልል ባለስልጣን የነበሩትና ከነቤተሰባቸው ሲጓዙ በተከፈተባቸው ጥቃት የተገደሉት የአቶ ግርማ የሺጥላ የአስከሬን ሽኝት እሑድ ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚከናወን የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ገለጸ፡፡

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በወላጆቻቸው ፍላጎት እና ጥያቄ መሰረት በተወለዱበት ሰሜን ሸዋ ዞን ማሀል ሜዳ  እንደሚፈጸም ተገልጿል።

የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው  በሰጠው መግለጫ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ የተፈጸመው ድንገተኛ ግድያ እንዳሳዘነው በመግለጫው ገልጾ ድርጊቱ የሚወገዝ ነው ብሏል፡፡

የሰኔ 15 የልብ ስብራት ሳይጠገን ሌላ ስብራት መከሰቱ አሳዛኝ ነው ያለው የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ወንድምን በመግደል አሸናፊ መኾን አይቻልም፤ የድል ባለቤትም አያደርግም ነው ያለው፡፡ የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ድርጊቱ የሕዝቡን ባሕል እና ሥነልቦና የማይመጥን እንደሆነ ገልጿል፡፡

የአማራ ሕዝብ በባሕሉ መሪውን ይጠብቃል ይንከባከባል፤ አልመራኝም ብሎ ሲያስብም እንዳይመራው ያደርጋል እንጅ ሰው እንዲሞት አይፈቅድም ነው ያለው የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ድርጊቱ ሀገርንም ክልሉንም እንደሚጎዳ አብራርቷል።

ድርጊቱ ከተሰማ በኃላ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከፍ ባለ ሁኔታ እንዲፈጸም የተለያዩ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን አስረድተዋል፡፡

ዋናው ኮሚቴ በክልል ደረጃ መዋቀሩን የገለጸው ኮሚቴው የቀብር ቦታው በወላጆቹ ፍላጎት እና ጥያቄ መሰረት በተወለደበት ሰሜን ሸዋ ዞን ማሀል ሜዳ እንዲኾን ፍላጎት በመኖሩ ሌላ ኮሚቴም እንዲዋቀር መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

ቀብሩ ወደ ትውልድ ቀየው ከመሄዱ በፊት በአዲስ አበባ የሽኝት ፕሮግራም እንደሚኖር የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው አስረድቷል፡፡

የሽኝት ፕሮግራሙም በወዳጅነት አደባባይ ባልደረቦቻቸው፣የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ወዳጅ እና ዘመዶቻቸው በተገኙበት እንደሚከናወን ነው ተጠቁሟል።

የሽኝት ፕሮግራሙም እሑድ ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋት ከ1ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ገልጾ በፕሮግራሙ ላይ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲገኙ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ለነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት እንዲያሳርፍ እና ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን እንዲያድል ተመኝቷል፡፡

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.