የኢትዮጵያና መሪና የፑቲን የሴንት ፒተርስበርግ ምክክር

  • 2ኛው የሩሲያ- አፍሪካ ጉባኤ ነገ ይጀምራል

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር ውይይት አካሂዷል።

የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ከባለስልጣኖቻቸው ጋር በሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሴንት ፒተርስበርግ የገባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራውን የኢትዮጵያ ልዑክ ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሩሲያ ወንድም ሀገር ነች ሲሉ ተናግረዋል።

የሁለትዮሽ ግንኙነታችን ለማሳደግና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ከወንድማማች አገራችን ጋር ለመወያየት ከፍተኛ ፍላጎት አለን ብለዋል።
በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ስገኝ ይህ የመጀመሪያዬ ነው፤ በጣም ቆንጆ ከተማ ነው ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል በባህል፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ ያለውን ግንኙነት ከፍተኛ ነው፤ የረዥም ጊዜ ግንኙነት አለን ብለዋል።
አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አብረን አሳልፈናል እናም ይህ ጉብኝት ግንኙነታችንን ለማጠናከር ይረዳል ብዬ አምናለሁ ሲሉም ነው ዶክተር ዐቢይ የተናገሩት። 
የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለረጅም ጊዜያት የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ በአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ ለመካፈል ከመጣው ልዑክ ጋር ጠቃሚ ውይይት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በጽሁፍ የተዘጋጀ ንባብ ያቀረቡት የሩሲያው መሪ ኢትዮጵያ አጋር አገር መሆኗን አንስተዋል። 

ከኢትዮጵያ መሪ ጋር ባደረጉት ውይይት ከጉብኝቱ ጋር ተያይዞ የመረጃና የኢነርጂ ጉዳዮችን ጨምሮ ሰፊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ለመድረስ የሚረዱ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መሪ ለተመራው ልዑክ ባደረጉት ንግግር ለጉብኝቱ አጠቃላይ የሰነዶች ፓኬጅ አዘጋጅተናል፤ ከነዚህም መካከል የኢንፎርሜሽን ደህንነት፣ የአየር ትራፊክን በተመለከተ፣ በኢንፎርሜሽና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች መስክ የመግባቢያ ሰነድ፣ በአቶሚክ ኢነርጂ አጠቃቀም ረገድ የትብብር ፍኖተ ካርታ፣ በጉምሩክ አገልግሎቶች መካከል የትብብር ፕሮቶኮል ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ወደሩሲያ ከተጓዘው ልዑክ መካከል የደህንነት ሃላፊው አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ከተገኙ ባለስልጣናት መካከል ናቸው። 
netevm.com