ኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ከሱማሌ ትራንስፖርት እና ሲቪል አቪየሽን ሚንስቴር ጋር በአቪዬሽን ዘርፉ በትብብር ለመስራት የሚረዳ ሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ኢትዮጵያ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚንስተር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን የሁለቱን አገራት ትብብር በማጠናከር ጉልህ ሚና ያለውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስተቸው ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ሶማሊያ ትራንስፖርት እና ሲቪል አቪየሽን ሚንስትር ፌርዶዋስ ኦስማን በበኩላቸው ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ብቻ ሳይሆን ሱማሊያ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ልምድ እንዲትቀስም የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በበለጠ የሚያጠናክርና የአገራቱን የልማት ዕቅድ ለማሳካት የሚረዳ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ስምምነቱ በተፈረሙበት ወቅት እንደገለጹት፤ የአቪዬሽን ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነቶች በቱሪዝምና በንግድ ዘርፍ በተለይ እንደሚያጠናክረው አስረድተዋል።
በትራንስፖርቱ የነበሩ ውስንነቶችን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ስምምነት መሆኑንም አስረድተዋል።
በተጨማሪ ስምምነቱ ዓለማቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን ቁጥር ለማሳደግ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ የአየር ትራንስፖርቱ የወጪ ንግዱን በመደገፍ፣ ቱሪዝምን በማስፋፋት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በውጭ ምንዛሪ ግኝት በአጠቃላይም ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገልጿል።