የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶው ለሽያጭ ቀረበ

በኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉትን ዋነኛው የመንግስት ቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ የሆነው የኢትዮ-ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ሊሸጥ ነው።

በኢትዮጵያ ሶስተኛውን የቴሌኮም አግልግሎት ፍቃድ  በማውጣት ወደ ገበያው መግባት  ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይፋዊ መግለጫ ወጥቷል።

በኢትዮጵያ ለቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የመስጠት ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ባልቻ ሬባ የፍላጎት ማሳወቂያው ጥሪው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ድርስ ለአንድ ወር እንደሚቆይ አስታውቀዋል።

 በአንድ ወር ውስጥ ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች ከባለስልጣኑ ጋርና ከአማካሪው ድርጅቱ ጋር መወያያትና መመካከር እንደሚችሉ ገልጸው ለዚህም የሚረዳ የምክክር ሰነድና ግብረ መልስ መስጫ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮ-ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ መግዛት የሚፈለጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የፍላጎት ማሳወቂያውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።

ለሶስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት መወዳደር የሚፈልጉ ድርጅቶች ደግሞ የፍላጎት ማሳወቂያውን ሰነድ  ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን  ድረ-ገፅ ላይ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለመግዛትና ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥሪ በቀረበበት መግለጫ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ከፊል የኢትዮ-ቴሌኮም ሽያጭ ክንውን  ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰኑን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ምቹ ሁኔታ በመኖሩ ፍላጎት ላላቸው ተጫራቾች ጥሪ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ በተመለከተም መንግስት ሶስት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ እንዲኖሩ በወሰነው መሰረት ከኢትዮ-ቴሌኮምና ከሳፋሪኮም በተጨማሪ ሶስተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ እንዲሳተፍ በአሁኑ ወቅት መጋበዙንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በይፋዊ የፍላጎት ማሳወቂያ መግለጫው ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስተር ዴኤታው ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ የኢትዮ-ቴሌኮም ከፊል ሽያጭና የሶስተኛው የቴሌኮም አግልግሎት ሰጪ ፍቃድ የማውጣት ሂደት የመንግስት የቴሌኮም ዘርፍ የማሻሻያ ዕቅድ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።

 የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያው የኢትዮ ቴሌኮምን የሚያጠናክር፣ ዘርፉን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ክፍት የሚያደርግና የዲጂታል ኢኮኖሚውን የሚያጎለብት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.