ኤፍ.ቢ.አይና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ የስራ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

የሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ተቋም ልዑካን ቡድኑ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ ገብቷል

የአሜሪካው የፌዴራል ቢሮ ኦፍ ኢንቨስቲጌሽን (ኤፍ.ቢ.አይ) የዓለም ዓቀፍ የኦፕሬሽን ዲቪዥን ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሬይሞንድ ዱዳ እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ትሬሲ አና ጃኮብሰን በኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው የስራ ጉብኝት አድርገዋል።ጠ

የአሜሪካው ኤፍ.ቢ.አይና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ  በቀጣይ ግንኙነታቸውን የበለጠ አጠናክረው በሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ አብረው ለመስራት የሚረዳ ውይይተ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከምክትል ዳይሬክተሩ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችን ገልጸዋል።

የኤፍ.ቢ.አይ የዓለም ዓቀፍ የኦፕሬሽን ዲቪዥን ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሬይሞንድ ዱዳ በበኩላቸው፣ ኤፍ.ቢ.አይ በድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዙሪያ ማለትም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ በውይይቱ ወቅት አንስተው ትብብሩን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ኤፍ.ቢ.አይ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ በአቅም ግንባታ ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ እና የፎረንሲክ ዲፓርትመንቱንም በማቴሪያል ለመደገፍ ቃል መግባታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በሶማሊያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ማሀድ ሞሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ መግባቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ተቋም ልዑካን ወደኢትዮጵያ ገባ

የሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ተቋም ልዑካን ቡድኑ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ወደኢትዮጵያ ተጉዟል።

ልዑኩ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።

የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ቆይታው የሀገሪቱን የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ይጎበኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።

ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረጉ የመረጃ ልውውጦች፤ በአቅም ግንባታ መስኮች፤ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ የጋራ ስምሪቶች ዙሪያ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮች ጋራ ምክክር እንደሚደረግም ተገልጿል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.