የኢትዮጵያ ጦር አዛዥና የሕወሓት ታጣቂ አዛዥ የኬንያው የስምምነት ፊርማ

ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ስምምነት ዝርዝር አተገባበርን በተመለከተ የመንግሥት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ እና የህወሓት ታጠቂዎች የጦር አዛዥ ዛሬ ማምሻውን በናይሮቢ ኬንያ ስምምነት አድርገዋል።

ስምምነቱን በፌዴራል የኢትዮጵያ መንግስት በኩል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና በሕወሓት በኩል ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች በተገኙበት ሲፈርሙ የፕሪቶሪያው ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ ስምምነት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ የትጥቅ መፍታትንና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ጉልህ እርምጃ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ተናግረዋል።

የዛሬው ፊርማ ፕሪቶሪያ ላይ ከአንድ ሳምንት በፊት ለተፈረመው ስምምነት ተግባራዊነት ለማድረግ የሚረዳ መሆኑ ይታመናል።

ለአምስት ቀናት በተደረገው ንግግር ላይ የፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ተጠቂዎች ዋና አዛዥ ታደሰ ወረደ በዋናነት ተሳትፈውበታል።

በመንግሥት እና ህወሓት መካከል ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈራረሙን ስምምነት ተከትሎ ነው ወታደራዊ አዛዦቹ የአፈጻጸም ሂደቱን በተመለከተ ከስምምነት የደረሱት።

ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት በዘላቂነት ግጭትን ማስቆም፣ የእርዳታ አቅርቦት እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች መጀመር እንዲሁም ትጥቅ መፍታትን የሚያካትት ነው።

ናይሮቢ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ንግግር ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው አጠቃላይ ስምምነት ተግባራዊ በሚደረግበት ዝርዝር ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ፊርማቸውን ያኖሩት የሁለቱም ወገን ናይሮቢ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግበራዊ እንደሚያደርጉ እምነታቸው መሆኑን የገለጹት የኬንያው የቀድሞ መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው።

የስምምነቱን ግዴታዎች ያላከበረ አካል ዕቀባ ሊጣልበት እንደሚችል ኡሁሮ ጠቆም አድርገዋል።

የፌዴራል መንግስት ከፊርማው ስነስርዓት በኋላ በመንግስት ኮሙንኬሽን አገልግሎት በኩል ባወጣው መግለጫ ለስምምነቱ ተግባራዊነት አስፈላጊውን ሥራ እንደሚያከናውን አስታውቋል።

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.