በኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው አካላትን ያሳተፈው የጋዜጠኞችና ሚዲያ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ጋዜጠኝነትን እና ዲሞክራሲን በተግባር ማጎልበት- ጥራት ያለው ጋዜጠኝነትን በመደገፍ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ጉባኤ የተሰናዳው ፎጆ – አይ ኤም ኤስ ኢትዮጵያ በተሰኘው ተቋም ነው።
ጉባኤው ከታህሳስ 6 እስከ 7 ፤ 2015 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩ በኢትዮጵያ ሚዲያ በሚታዩ ለውጦች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይነት ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል።
የኦንላየን ሚዲያና የሃሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ ሂደቶች፣ የሚዲያ ተቋማት ጫና፣ የፋይናንስ ፈተናዎች፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማለፍ የሚረዱ መንገፈዶችና ልምዶች እንዲሁም በሚዲያዎች በኩል ትብብር የመስራት ልምድን ለማዳበር የሚረዱ ሂደቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በጉባኤው የሚዲያ ባለድርሻ አካላት የሆኑ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ባለቤቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የሚዲያ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖችን ጨምሮ 100 የሚጠጉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
የሚዲያ ማሻሻያዎችን ለመደገፍ በአጋርነት የሚመራ ብሔራዊ የሚዲያ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት ጥረት የተደረገበት መድረክ ሆኗል።
የሚዲያ ማሻሻያ ሂደቱ በስፋት ተደራሽ፣ ክፍት እና ሰውን ያማከለ እና ሁለንተናዊ እሴቶች እና መሰረታዊ መብቶችን ያገናዘበ ሆኖ እንዲቀጥል ባለድርሻ አካላት ተወያይተዋል።
በተመሳሳይ በጉባኤው የሚዲያ ማሻሻያ፣ ሙያዊ ብቃትና አካታችነት የተዳሰሰበት ሲሆን፤ ለችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ጉባዮች ወደተጨባጭ ፖሊሲዎችና ተግባራት እንዴት መተርጎም እንደሚቻል የተመላከተበት ነው።
ፎጆ የአይ ኤም ኤስ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ሶፊ ጉልልበርግ ጉባኤው በኢትዮጵያ ያለውን የጋዜጠኞች አቅም ለማጎልበትና ዴሞክራሲን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑን በመድረኩ ተናግረዋል።
ፎጆ የአይ ኤም ኤስ ፕሮግራም ኦፊሰር ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው፤ ሚዲያዎች በጋራ በመስራት የተሻለ ለውጥ የሚያመጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የሚዲያ ስራ ከማሳደግ ባለፈ በቀጣይ በሚከናወኑ የአገራዊ ምክክረ ኮሚሽን ስራዎች ላይ የሚዲያዎች ስራ የህዝቡን ጥቅም የሚያሳድግ እንዲሆን የሚረዳ ጥምረት ለመፍጠር ጉባኤው አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጥራት ያለው የጋዜጠኝነት ስራና የሚዲያ አቀራረብ ለአንድ አገር ዕድገትና ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት አስገፈላጊ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በዚህ ረገድ ፎጆ የአይ ኤም ኤስ ፕሮግራም የበኩሉን ሚና ለመወጣት ጉባኤውን ማሰናዳቱን ገልጸዋል።
በጉባኤው በኦንላይም ሚዲያና ቴክኖሎጂ ልምድ ያላቸው የኢትዮጵያና የኬንያ ጋዜጠኞች ልምዳቸውን አጋርተዋል።
የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ፣ የኢትዮጵያን ኢንሳይደር ሚዲያ ስራ አስኪያጅ ተስፋለም ወልደየስ፤ የገበያኑ ሚዲያ ባለቤት ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ፣ የተለያዩ መጽሔቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ታምራት ሃይሉ እና ሌሎችም በርካታ የሚዲያ ተዋናዮች በጉባኤው ተሳትፈዋል።
በአዲስ አበባ የተካሄደውን ጉባኤ ያዘጋጀው ፎጆ አይ ኤም ኤስ (IMS –FOJO) ቀደም ሲል ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው ዊውተርስራንድ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮረ ጉባኤ ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።