ኢንስፔክተር አብዲ ሰይድ እና አሸብር ተስፋዬ ሀምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከግብረአበሮቻቸው ጋር የፌዴራል ፖሊስ ልብስ በመልበስና በመሳሪያ በማስፈራራት ንብረት መዝረፋቸውን ያስታወሰው ፍርድ ቤት በጽኑ እስራት ቀጥቷቸዋል።
በኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ወንጀለኞቹ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶችን ከግለሰብ ቤት አስፈራርተው የዘረፉ መሆኑን በመግለጽ በተሰወሩ ተከሳሾች በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እና 12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አንደኛ አሸብር ተስፋዬ እና ሁለተኛ ኢንስፔክተር አብዲ ሰይድ፣ የተባሉት ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ሃብት ለማግኘት በማሰብ ወንጀል ሰርተዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ክልል ልዩ ቦታው ኩኑዝ ኮሌጅ ጀርባ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ልብስ በመልበስና የጦር መሳሪያ በመያዝ ካልተያዙት ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን 1ኛ ተከሳሽ የጦር መሳሪያ በማውጣት 1ኛ እና 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ላይ ብትናገሩ እተኩስባችኋለሁ በማለት አስፈራርተዋል።
በተለምዶ ዶልፊን እየተባለ የሚጠራውን ተሽከርካሪ የግል ተበዳይ በር ላይ አቁመው ኢንስፔክተሩ የግል ተበዳይን የውጭ በር በሀይል አንኳኩቶ በመግባት በግቢ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች አንድ ክፍል ውስጥ እንዲቆለፍባቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል ሲል ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
የዶልፊኑ ሾፌር እና 1ኛ ተከሳሽ ከቤት ውስጥ ሽጉጥ፣ የጣት እና የአንገት ወርቆች፣ቴሌቪዢን፣ የውስኪ መጠጦች፣የሞባይል ቀፎዎች፣ጥሬ ገንዘብ ከነካዝናው፣ በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 1 ሚሊዮን 224 ሺ ብር የሚያወጡ ንብረቶችን ይዘው ተሰውረዋል።
ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በከባድ የውንብድና ወንጀል በዐቃቤ ህግ በቀረበባቸው ክስ መሰረት ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ክርክሩን የመራው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዐቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው 4 ተከሳሾች መካከል የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በበቂ ሁኔታ ያስረዱባቸውን 2 ተከሳሾች በተከሰሱበት የከባድ ውንብድና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው አግኝቷል።
በቅጣት አወሳሰን መመሪያ 2/2006 መሰረትም በወንጀል ደረጃ 4 እርከን 36 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን በ1 ማቅለያ በመያዝ በእርከን 35 ስር በማሳረፍ፣ በ3ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበበት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተጨማሪ በማረሚያ ቤት የሰላም ኮሚቴ በመሆን እያገለገለ የሚገኝ መሆኑ፣ የአስም ታማሚ መሆኑና እንዲሁም ለህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ለሀገር ልማት አስተዋፅኦ ያደረገ በመሆኑ 5 ማቅለያዎች ተይዘውለት በእርከን 31 ስር አሳርፎታል።
በአጠቃላይ አሸብር ተስፋዬ በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና 2ኛ ተከሳሽ ኢንስፔክተር አብዲ ሰይድ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡