ጣና እና በጣና ዙሪያ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ለምን ተጣጥመው አልሄዱም?

የጣና ሐይቅ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሐይቆች ትልቁና ዋነኛው የቱሪስት መስህብ ነው። በሐይቁን በሚገኙ አነስተኛ ደሴቶች ላይ የተመሰረቱ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ለበርካታ ሺህ ዘመናት የሐይቁን ብዝሃ ሕይወት ሳይጎዱ አካባቢውን እያለሙ ተጣጥመው ቆይተዋል።

ይሁንና ድፍን 50 ዓመት እንኳን ያልሞላቸው በጣና ዙሪያ የተገነቡ ሆቴሎችና የተለያዩ ድርጅቶች ግን ከሐየቁ ጋር ተቃርኖ ውስጥ እንዳሉ በሚመስል ሁኔታ ብዝሃ ሕይወቱን ከመጠበቅ ይልቅ የሚጎዱ ተግባራትን በስፋት ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

ቆሻሻቸውንና የተለያዩ ኬሚካሎችን እንዲሁም ሐይቁን ሊጎዱ የሚችሉ ንጠረ ነገሮችን በድብቅ ማስወገጃዎቻቸው በኩል በመልቀቅ ለዓመታት ጥፋትን ሲያከናውኑ የቆዩ ድርጅቶች መኖራቸው ገሃድ የወጣ ጉዳይ ነው።

ይህ ጥፋት ባልቆመበት ሁኔታ ላይ ደግሞ ጣና ተጨማሪ አደጋ ደረሰበት፤ በእንቅርት ላይ እንዲሉ በበርካታ አገራት ጥፋት ያደረሰው እንቦጭ አረም ሐይቁን በመውረር ጉዳት እያደረሰበት ይገኛል።

ምን ያክሉ በጣና ዙሪያ የተገነቡ ድርጅቶች እንቦጭን ለመከላከልና የሐይቁን ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅ የሚጠበቅባቸውን ጥረት አደረጉ የሚለው ጥያቄ ሲነሳም፤ ምለሱ አጥጋቢ አይደለም።

ችግሩ ላይ ምልከታ ያደረገ በጣና ሃይቅና አካባቢው ጥበቃና ዘላቂ ልማት ላይ የሚደረግ የባለድርሻ አካላት ምክክርም መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በአቫንቲ ብሉናይል ሆቴልተካሂዷል።

በአብክመ ጣና ሃይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲና ናቡ ኢትዮጵያ በተሰኜ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት የተዘጋጀው የምክክር መድረክ  ላይ የአማራ ክልል አመራሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋምት ምሁራንና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

በምክክር መድረኩም የጣና ሃይቅና አካባቢው ዘላቂ ልማትና ጥበቃን በተመለከተ ሰፊና ጠቃሚ ውይይት ተደርጎበታል፡፡  በተለይም በሐይቁ አካባቢ በሚከናወኑ የቱሪዝማ የኢንቨስትመንት ልማቶች አማካኝነት ወደጣና ስለሚለቀቁ መርዛማ ንጠረነገሮችና ጎጂ ተረፈ ምርቶች ጥፋት እያደረሱ ስለመሆኑ ውይይይት ተደርጓል።

የጣና ሃይቅና በክልሉ በሚገኙ የውሃ አካላት እንዲሁም ውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለመጠቀም ያጋጠሙ ችግሮችና አማራጭ መፍትሄዎችን በተመለከተ ዘርዘር ያለ ሃሳብን ለታዳሚዎች ቀርቧል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ዶ/ር ጌታቸው  ጀምበር በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ ያለው እንቦጭ አረም እና ወደ ሐይቁ በጎርፍ አማካኝነት የሚገቡ ኬሚካሎች ሐይቁ ላይ ጉዳት እያደረሱ መኾኑን ገልጸዋል።

ጣና አጠገብ የተገነቡ ኢንቨስተመንቶች በተለይም ሆቴሎች በሐይቁ የሚጨምሯቸውን የተለያዩ መርዛማ ኬሚካሎችና ዝቃኞችን ለመከላከል በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት ይተላለፋል። ከዚህም በተጨማሪ ጥፋቱ ሲገኝ ቅጣት እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

የጣና ሃይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር  ዶ/ር አያሌው ወንዴ  ደግሞ የብዝሃ ሕይወቶች መገኛ የሆነውን ጣናን መጠበቅ ግዴታችን ነው ብለዋል።  

በጣና ዙሪያ ላይ ለማልማት የተዘጋጁ ባለሃብቶች እንዲሁም ካሁን በፊት የገነቡ ባለሀብቶች የሸይቁን ደህንነትና ብዝሃ ሕይወቱን ለመጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍና መተግባር እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጣና ሃይቅ የሁላችንም ስለሆነም ሁሉም አካላት የጣና ልማትንና ጥበቃን በተመለከተ ሊረባረብ ይገባዋል ሲሉ ዶክተር አያሌው ተናግረዋል።

ጣናን ለመታደግ በማህበረሰቡና በሚመለከታቸው አካላት እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸውና ለዚሁም የአብክመ የጣና ሃይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት አጄንሲም ጣናን ለመታደግ ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ጥረት እያደረገ ነው ነገር ግን የበጀት ድጋፍ ያስፈልገዋል ሲሉ አሳስበዋል።

ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ በበኩላቸው የጣና ሃይቅን ጤንነትና ዘላቂ ጥቅም ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ ሊደረግበት እንደሚገባና ጣናን ለመታደግ የሚጠቅም ሕግ ሊወጣለት ይገባል ብለዋል፡፡                

netevm.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.