ኢሰመኮ በመዲናዋ ትምህርት ቤቶች የታየውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ አሳሰበ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት በሚሰጥባቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘመር ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ያደረገውን ምርመራ አሳውቋል።
ውሳኔውን በሚቃወሙ እና በሚደግፉ ተማሪዎች መካከል በተከሰተው ውዝግብና ግጭት ምክንያት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ያስከተለውን የሰብአዊ መብቶች እንድምታ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
ምንም እንኳን የጸጥታው ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ ጋብ ያለ ቢሆንም፤ ለወደፊቱም ይህን መሰል ሁኔታዎችንና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በዘላቂነት ለመከላከል እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትልና ምርመራ የተረጋገጡ ግኝቶችን፣ ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው የሕግ ማዕቀፎች አንጻር በመተንተን ጭምር ይህን ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራና ክትትል የጸጥታ መደፍረስ የተከሰተባቸውን ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የሚሸፍን ምርመራ ለማካሄድ ባይቻልም፤ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን፣ መምህራን እና ኃላፊዎችን፣ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የነበሩ ተማሪዎችንና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን አነጋግሯል።
የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የነበሩ ምስክሮችንና የተማሪዎች ወላጆችን እንዲሁም የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሌሎች ኃላፊዎችን በማነጋገርና መረጃዎችና ማስረጃዎች በማሰባሰብ ስለ ጠቅላላ ጉዳዩ ተገቢውን ግንዛቤ ለማግኘት መቻሉን ገልጿል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደፊትም እንዳያጋጥሙ ለችግሩ መንስኤ ለሆነው የሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብ ሕፃናትን ጨምሮ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ግልጽ የሆነ የሕግ እና ፖሊሲ መፍትሔ በማበጀት ዘላቂ እልባት በሊሰጠው ይገባል ብሏል።
በተጨማሪ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች እና የሰብአዊ መብቶች መርሆችን በማክበርና በማስከበር የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በጋራ እንዲከላከሉ አሳስቧል።
ከዚህ ባለፈ የየትምህርት ቤቶቹና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በሰላም፣ በመቻቻል እና የሃሳብ ልዩነትን በመቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመፍታት ላይ ተመሥርቶ የመፍትሔ አካል እንዲሆን አበክሮ አሳስቧል፡፡